Friday, December 31, 2010

ነገረ ቅዱሳን ክፍል ፰

         ሙሴ ከነገደ ሌዊ ሲወለድ፦ እስራኤል በግብፅ በባርነት ነበሩ። ዘጸ ፪፥፩። ይህ ጊዜ እስራኤላውያን እናቶች ወንድ ልጅ ከወለዱ እንዲገደል በግብፅ ንጉሥ የታዘዘበት ጊዜ ነበር። ሙሴ ሲወለድ ብርሃን ተሥሎበት ነበርና፦ አዋላጆቹ ራርተው ይህንስ የፈጠረው ይግደለው ብለው ትተውታል። እንድም፦ ቅዱስ ጳውሎስ እንደመሰከረው « ሙሴ ከተወለደ በኋላ ወላጆቹ ያማረ ሕፃን (በፊቱ ላይ ብርሃን የተሣለበት) መሆኑን አይተው ፦ በእምነት ሦስት ወር ሸሸጉት ፥ የንጉሡንም አዋጅ አልፈሩም።» ዕብ ፲፩፥፳፫። ከሦስት ወር በኋላ ግን ወንድ መሆኑ በልቅሶው በሳሉ ስለሚታወቅ ፦ በሳጥን አድርገው፥ እግዚአብሔር ያነሣዋል ብለው፥ ከአባይ ወንዝ ዳር በቄጤማ ውስጥ አስቀመጡት። ቀን ቀን እኅቱ ትጠብቀዋለች ፥ ሌሊት ሌሊት ደግሞ እናቱ ስታጠባው ታድራለች። ዘጸ ፪፥፩-፫።
፫፥፩፦ የእግዚአብሔር ሥራ በሕፃኑ ላይ፤
          ተርሙት የምትባል የፈርዖን ሴት ልጅ፦ ልትታጠብ ፥ አንድም ፦ ከብሽ የሚባል ደዌ ነበረባትና ልትጠመቅ ፥ አንድም፦ ነጋዴ ወዳጅ ነበራትና እርሱን ለመቀበል ፥ አንድም፦ አዞ ጉማሬ ታመልክ ነበርና ስለዚህ ፥አንድም፦ የውኃ ዋና ልትማር ወደ ወንዝ ወረደች። ደንገጡሮቿ በወንዝ ዳር ይመላለሱ ነበር። እነርሱ ሳያዩ እርሷ ሳጥኑን አሻግራ በቄጤማ ውስጥ አየች። ደንገጡሯንም ልካ አስመጣችው። ነጋዴ የረሳው ዕቃ መስሏት ነበር። በከፈተችው ጊዜ ግን የሚያለቅስ ሕፃን ሆኖ አገኘችው ፥ እግዚአብሔር ልቧን ስላራራው አዘነችለት። ምነው የኔ ልጅ በሆነ ብላም ተመኘች። ደንገጡሯም ምኞቷን ሰምታ ፥ «እመቤቴ፦ አሁንስ ወለድኩ ብትዪ ይሆን የለምን፤» አለቻት። እርሷም ፦ «ማርገዜ ሳይታወቅ ወለድኩ ብል ማን ያምነኛል?» አለች። ደንገጡሯም ፦ «የነገሥታት ልጆች በእልፍኝ ትኖራላችሁ ፥ መውለዳችሁ ነው እንጂ ማርገዛችሁ ይታወቃልን?» ብላ መለሰችላት። በዚህን ጊዜ በስውር ትጠብቀው የነበረች እኅቱ ማርያም፦ «ሕፃኑን ታጠባልሽ ዘንድ ሄጄ የምታጠባ ሴት ከዕብራውያን ሴቶች ልጥራልሽን?» ብትላት ፈቃደኛ ሆነች። ሄዳም እናቱን አመጣች። የፈርዖንም ልጅ፦ እናቱን ፦ « ይህን ልጅ ተንከባክበሽ ፥ ጠብቀሽ አሳድጊልኝ፤ እኔም የአሳዳጊነት ዋጋሽን እሰጥሻለሁ።» አለቻት። የትም ብንወድቅ ፥ የትም ብንጣል እግዚአብሔር እንዲህ ያነሣናል። ዘጸ ፫፥፬-፮።

፫፥፪፦የሙሴ አስተዳደግ፤
          በስመ ሞግዚት ልጇን መልሳ ያገኘች የሙሴ እናት በጥሩ ኹኔታ አሳደገችው። ስታሳድገው እንዲያው (ጡት በማጥባት ፥ ፍትፍት በማጉረስ ብቻ) አይደለም። «ተስፋ ያልተነገረላቸው የእነዚህ የቈላፋን (የኢግዙራን) ልጅ አይደለህም። ተስፋ የተነገረላቸው የአብርሃም ፥ የይስሐቅ ፥ የያዕቆብ ልጅ ነህ፤» እያለች አሳድጋዋለች። አባቱም ሁልጊዜ ዜና አበውን ይነግረው ነበር። በዚህም አጠቃላይ ማንነቱን ማለትም ፦ ሃይማኖቱን ፥ ሥርዓቱን ፥ ባሕሉን ፥ ታሪኩን ፥ ተስፋውን፥ አውቆ አደገ። ከዚህ በኋላ ወስዳ ለፈርዖን ልጅ አስረከበችው። እርሷም፦ «እኔ ከውኃ አውጥቼዋለሁና፤» ስትል ሙሴ አለችው። የንጉሥ የልጅ ልጅ ተብሎ በምቾት አደገ። ምቾቱ ግን ማንነቱን አላስረሳውም። ዘጸ ፫፥፯-፲።
፫፥፫፦ ሙሴና ወገኖቹ ፤
          ሙሴም የአርባ ዓመት ጐልማሳ ከሆነ በኋላ ወንድሞቹ እስራኤል ወደ አሉበት ወደ ራምሴ  በሄደ ጊዜ ግብፃውያን የሚሠሩባቸውን ግፍ አይቶ ፈጽሞ አዘነ። ብዙ ሰው ግን እርሱ ከተመቸው ማንም ትዝ አይለውም። ሙሴ አንድ የግብፅ ሰው ፦ የወንድሞቹን የዕብራውያንን ሰው ሲመታው አየ። የመታው በመስኖ ውኃ ምክንያት፦ አንድም ዕብራዊው ያጠመደውን ዓሣ ልውሰድብህ ብሎት ፥ አንድም ዕብራዊው በዘረጋው ጃንዲ በበጠበጠው እንዶድ ልጠብበት ብሎ ነው። ከዚህም አልፎ በገላህ ፥ በደምህ ባጥብ በገዛ ባሪያዬ ማን ከልክሎኝ ብሎታል። በዚህን ጊዜ ሙሴ፦ ግብፃዊውን ገድሎ በአሸዋ ውስጥ በመቅበር ለወንድሙ ተበቅሎለታል። ይህም ክርስቶስ የዲያቢሎስን ሥራ ገድሎ አዳምን ነፃ ለማውጣቱ ምሳሌ ነው። ብዙ ሰዎች ወንድማቸው ሲበደል አይተው እንዳላዩ፥ ሰምተው እንዳልሰሙ፥ ይሆናሉ። ወይም የኃይል ሚዛኑን አይተው ከበዳይ ጋር ይሰለፋሉ። ዘጸ ፪፥፲፩።

፫፥፬፦ የሙሴ ስደት፤
          በበነጋው በራምሴ ፥ በጋምሴ ያሉትን ዘመዶቹን ጠይቆ ሲመለስ ሁለት ዕብራውያን ሲጣሉ አገኘ፤ ሙሴም በዳዩን ቀርቦ፦ «ለምን ወንድምህን ትመታዋለህ?» አለው። ያም ሰው፦ «በእኛ ላይ ፈራጅ ዳኛ አድርጎ የሾመህ ማነው? ወይስ ትናንት ያን ግብፃዊ እንደገደልከው እኔንም ልትገድለኝ ትወድለህን?» አለው። ሙሴ ግብፃዊውን የገደለው በሥውር ቢሆንም፦ « አመስጋኝ አማሳኝ፤» እንዲሉ፦ ያ ያዳነው ሰው ፦ « ትናንት ወንድሜ ሙሴ ባያድነኝ ኖሮ ግብፃዊው ገድሎኝ ነበር።» ብሎ ሲናገር ሰምቶ ነው። የሙሴን ምክር የገዛ ወገኑ አለመቀበሉ ፥ ክርስቶስን የገዛ ወገኖቹ አይሁድ ላለመቀበላቸው ምሳሌ ነው። « ወደ ወገኖቹ መጣ ፥ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም፤» ይላል። ዮሐ ፩፦፲፩።
          ሙሴም ያደረገው ነገር ሁሉ እንደተሰማበት አውቆ ፈራ፥ ፈርዖንም ይህን ነገር ሰምቶ ሊገድለው ወደደ። በዚህ ምክንያት ወደ ምድያም አውራጃ ተሰደደ። በመንገደኛ ልማድ ፦ ጥሬ ቆርጥሞ ፥ ውኃ ጠጥቶ ለመሄድ ከውኃ ዳር ተቀምጦ ሳለ፦ የዮቶር ሰባት ሴት ልጆች በጎቻቸውን ማጠጣት ጀመሩ። በዚህን ጊዜ ሌሎች እረኞች መጥተው ተጋፉአቸው። ሙሴ ይህን አይቶ ዝም አላላም። ሁልጊዜም ለተገፉት መቆም ልማዱ ስለሆነ «ግዳይ ላፈለመ ፥ ውኃ ለቀደመ ነው ፤» ብሎ ሴቶቹን ረዳቸው፥ በጎቻቸውንም አጠጣላቸው። ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ፥ ፈጥነው የተመለሱበትን ምክንያት አባታቸው ቢጠይቃቸው የሆነውን ሁሉ ነገሩት። እርሱም ፦ « እንዲህ ያለውን ሰው፦ ለምን ትታችሁ መጣችሁ? አሁንም ጥሩትና እህል ይቅመስ፤ » አላቸው። በዚህን ጊዜ ፦ ሲፓራ የተባለች ልጁ፦ «አሁንም አላጣውም ፥ ልሂድ ፤» ብላ ይዛው መጥታለች። ይህም የወደፊት ባሏ የሚሆን ነውና ፈቃደ እግዚአብሔር አነሣሥቷት ነው። መልአከ እግዚአብሔርም እየመራ ከዚያ አድርሷታል።
          ሙሴ አንድ ቀን አድሮ በበነጋው ፦ « ልሂድ አሰናብተኝ፤» ቢለው፦ እርሱም «የት ትሄዳለህ?» አለው። ሙሴም፦ «እግሬ ካደረሰኝ ፤» አለው። እርሱም፦ «ውኃ ቢቀዱት ቢቀዱት ፥ መንገድ ቢሄዱት ቢሄዱት ያልቃልን ? ለኔ ወንድ ልጅ የለኝምና ከእነዚህ ከልጆቼ አንዲቱን አግብተህ ፥በጎቼን እየጠበቅህ ፥ ተቀመጥ፤» ብሎት፥ በዚህ ተዋውለው ፥ሚስት ልትሆነው ሲፓራን ሰጥቶታል። ዘዳ ፪፥፭-፳፪።
፫፥፭፦ የእግዚአብሔር ጥሪ፤
          ሙሴ በጎቹን አሳማርቶ ሳለ፦ እግዚአብሔር በእሳት ነበልባል አምሳል ሐመልማሏን ተዋሕዶ በደብረ ሲና ተገለጠለት። «ሙሴ ፥ሙሴ ሆይ፤» ብሎ፦ በክብር ጠርቶ አነጋገረው። የቆመባት ምድር የተቀደሰች በመሆኗ ጫማ ሳያወልቅ እንዳይቀርብ ከመንገር ጋር፦ «እኔ የአባቶችህ አምላክ፦ የአብርሃም አምላክ ፥የይስሐቅም አምላክ ፥ የያዕቆብም አምላክ ነኝ፤» አለው። የሕዝቡን መከራ አይቶ ፥ጩኸታቸውን ሰምቶ ፥ ሥቃያቸውን አውቆ ሊያድናቸው ፥ ማርና ወተት ወደሚያፈስሰው ምድር ሊያገባቸው እንደወረደ ፥ ለዚህም ሥራ እርሱን እንደመረጠው ነገረው። ሙሴ ዓለምን ንቆ በመመነኑ ፥ ከጌትነት ወደ ባርነት ፥ ከአለቅነት ወደ አሽከርነት በመውረዱ እግዚአብሔርን አገኘ። ከራሱ ምቾት ፥ድሎት ይልቅ የወገኖቹን መከራ በማስበለጡ እግዚአብሔርን በእሳት ምሳሌ አየው። እመቤታችንን ደግሞ ባልተቃጠለችው የሲና ሐመልማል ምሳሌ አያት። የምድራዊ ንጉሥ የልጅ ልጅ መባልን በእምነት እምቢ በማለቱ የሰማያዊ ንጉሥ ልጅነቱ ጸናለት። የምድራዊት እመቤት ልጅ መባልን በመናቁ፦ የራቀው ቀርቦ ፥ የረቀቀው ጎልቶ እመቤቱን በበረሃ ውስጥ በለመለመች ዕፅ ምሳሌ አገኛት። ይኽንን በተመለከተ ቅዱስ ጳውሎስ ፦ «ሙሴም በአደገ ጊዜ የፈርዖን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እምቢ አለ፤ ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ። የክርስቶስ የመስቀሉ ተግዳሮት ከግብፅ ሀብት ሁሉ ይልቅ እጅ የሚበልጥ ባለጠግነት መሆኑኑ አውቋልና ፥ ዋጋውንም ተመልክቷልና። የንጉሡንም ቊጣ ሳይፈራ ፥ የግብፅን ሀገር በእምነት ተወ፤ ከሚያየው ይልቅ የማይታየውን ሊፈራ ወዷልና።» ብሏል። ዕብ ፲፩ ፥፳፬-፳፯። እኛ ግን እግዚአብሔርን፥ እመቤታችንንም ለማየት የምንፈልገው ፥ ቤተ ክርስቲያንንም ለማገልገል የምንሮጠው፥ በሥጋ ፍላጐት ተውጠን ነው። ዘጸ ፫፥፩-፲።
፫፥፮፦ የሙሴ ትህትና፤
          ሙሴ ለዚህ ታላቅ ሹመት እግዚአብሔር ሲመርጠው ይገባኛል አላለም፦ «ይኽን አደረግ ዘንድ እኔ ማነኝ? እኔ ምን ቁም ነገር ነኝ?» አለ። እግዚአብሔርም፦ «በእውነት እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤» አለው። ሕዝቡ፦ «ማን ላከህ?» ሲለውም ፦ ምን ማለት እንዳለበት ለንጉሡም ምን መንገር እንዳለበት ነገረው። ከዚህም ጋር ተአምራታዊ ኃይልና ምልክት ሰጠው። ይህ ሁሉ ሆኖም፦ «ጌታ ሆይ ፥ እማልድሃለሁ፤» ትናንት ፥ ከትናንት ወዲያ ባሪያህን ከተናገርኸኝ ጀምሮ አፈ ትብ (አንደበተ ርቱዕ) ሰው አይደለሁም። እኔ አፌ ኰልታፋ ፥ ምላሴም ተብታባ የሆነ ሰው ነኝ፤» አለ። እግዚአብሔርም፦ «ለሰው አፍን የሰጠ ማን ነው? እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን? እንግዲህ አሁን ሂድ፤ እኔም አንደበትህን አረታለሁ፤ ትናገረውም ዘንድ ያለህን አለብምሃለሁ። (ልብ አስደርግሃለሁ)።» አለው። ሙሴም፦ «ጌታ ሆይ ፥ እማልድሃለሁ፤ ወደ ንጉሥ ቤት የሚላክ ነገር አከናውኖ የሚናገር ሰው ነው። እኔ ነገር አከናውኖ መናገር አይቻለኝምና ሌላ ሰው ፈልገህ ላክ፤» አለው። እግዚአብሔር በሙሴ ላይ እጅግ ተቆጥቶ ሌዋዊው ወንድምህ አሮን አለ አይደለምን? እርሱ እንደሚነግርልህ አውቃለሁ፤ እነሆም፥ እርሱ ገናኝህ ይመጣል፤ በአየህም ጊዜ ልቡ ደስ ይለዋል። አንተም ትነግረዋለህ፤ ቃሌንም በአፉ ታደርገዋለህ፤ እኔ አንደበትህንና አንደበቱን አረታለሁ፤ የምታደርጉትንም አለብማችኋለሁ። (ልብ እንድትሉ አደርጋችኋለሁ)። እርሱ ስለ አንተ ከሕዝቡ ጋር ይነጋገራል፤ እርሱ አፍ  ይሆንሃል፤ አንተም በእግዚአብሔር ንድ ትሆንለታለህ። ይህችንም ተአምራት የምታደርግባት በትር በእጅህ ያዝ፤» አለው። በመንፈሳዊውም ሆነ በሥጋዊው ዓለም  ከላይ እስከታች ለሥልጣን ብለን ለምንጋደል ሰዎች ይህ የሙሴ ሕይወት ለእኛ ታላቅ  ተግሣፅ  ነው። ዘጸ ፫፥፲፩ ፣ ዘጸ ፬፥፩-፲፯።
፫፥፯፦ የሙሴ ወደ ግብፅ መመለስ፤
ሙሴ ወገኖቼን ልጠይቅ ብሎ ዮቶርን ተሰናበተው ፥ እርሱም «በደኅና ሂድ፤» አለው። ከብዙ ዘመንም በኋላ ሙሴን ያሳደደው የግብፅ ንጉሥ ሞቶ ሌላ ተተክቶ ነበር። እግዚአብሔርም፦ «ነፍስህን የሚሹአት ሰዎች ሁሉ ሞተዋልና ወደ ግብፅ ሂድ፤» አለው። ይህም የእግዚአብሔር መልአክ ዮሴፍን፦ «የሕፃኑን ነፍስ የሚሹ ሙተዋልና ፥ ተነሥተህ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ሀገር ሂድ፤» ላለው ምሳሌ ነው።
          ሙሴ ጉዞ የጀመረው ሚስቱንና ሁለቱን ልጆቹን ይዞ ነበር። በመንገድ ላይ በአደረበት ስፍራ የእግዚአብሔር መልአክ አገኘውና ሊገድለው ፈለገ። ሙሴ አንዱን ልጁን የእኔ ፈንታ ነው ፥ ብሎ ሲገርዘው ፥ ሁለተኛውን ግን የእናቱ ፈንታ ነው ፥ ብሎ ትቶት ነበር። ሚስቱ ሲፓራም፦ በባልጩት (በድንጋይ ምላጭ) ፈጥና የልጅዋን ሸለፈት ከገረዘች በኋላ፦ «ይህ የልጄ የግርዛቱ ደም ስለ እርሱ ፈንታ ይሁን፤» ብላ ለመልአኩ ሰገደች። ሙሴም መልአኩን፦ «ምን አጠፋሁ?» አለው። መልአኩም፦ «ከግብፅ ያሉትን አውጣቸው፤ ብትባል ፥ ከዚህ ያሉትን ይዘህ ትሄዳለህ ? » አለው። ሙሴም፦ «እኔማ ማን ይመግባቸዋል ብዬ ነው?፤» አለ። መልአኩም፦ « እስኪ ከዚህ ባሕር እጅህን ስደድ ፤ » አለው። እጁን ቢሰድድ ደንጊያ ይዞ ወጣ። መልአኩም፦ «ስበረው፤» አለው። ቢሰብረው፦ አንድ እውር ትል መንታ ቅጠል ያላት እንጨት በቅሎለት  አንዲቱን እስኪበላ አንዲቱ እያደገችለት አየ። መልአኩም፦ «ይህን የሚመግብ ማነው?» አለው። ሙሴም፦ «እግዚአብሔር» አለ። መልአኩም፦ «ይህን የመገበ ይመግባቸዋልና ፥ ትተሃቸው ሂድ፤ » አለው። እርሱም ትቷቸው ሄደ። የእኛም ወላጆች ፦ «እውር አሞራ የሚመግብ አምላክ ያውቅልኛል፤» ይላሉ።
          አሮንም ከከተማው ወጥቶ እግዚአብሔር ሙሴን አግኘው ባለው ቦታ በእግዚአብሔር ተራራ አግኝቶት እጅ ነሣው፥ እርስ በርሳቸውም ተሳሳሙ። ሙሴም ሁሉንም ለአሮን ነገረው።  « ከሽማግሌ ምክር ፥ ከጎበዝ ረር ፤» እንዲል፦  የእስራኤልን ሽማግ ሌዎች ሰብስበው ነገሯቸው ፥ ሕዝቡም ፍጹም እስ.ከያምኑ ድረስ ተአምራት አደረጉላቸው። ዘጸ ፬፥፲፰-፴፩።
፫፥፰፦ ሙሴና አሮን በፈርዖን ፊት፤
          ሙሴና ኦሮን፡- እግዚአብሔር ልኳቸዋልና፡- ሳፈሩና ሳያፍሩ በንጉሡ ፊት ቆሙ። የእግዚአብሔርንም መልእክት ነገሩት። እርሱ ግን፡- «የእስራኤልን ልጆች እለቅቅ ዘንድ፥ ቃሉን የምሰማው እርሱ እግዚአብሔር ማነው? እግዚአብሔርን አላውቅም፥ እስራኤልንም ደግሞ አልለቅም፤» አለ። «የሦስት ቀን መንገድ ተጉዘው አምልኮታቸውን እንዲፈጽሙ እግዚአብሔር ጠርቷቸዋል፤» ቢሉትም፡- አልሰማም። «ለምን ይህን ሕዝብ ሥራ ታስፈቱታላችሁ፥ ሥራ የላችሁምን? ይልቁንስ ወደ ሥራችሁ ሂዱ፤» አላቸው። በሕዝቡም ላይ ከቀድሞው የበለጠ የሥራ ጫና እንዲደረግባቸው፥ መከራም እንዲጸናባቸው ሹማምንቱን አዘዛቸው። ሕዝቡም መከራው እንዲቀልላቸው ወደ ፈረዖን አቤት ብለው (አቤቱታ አቅርበው) መልስ በማጣታቸው ሙሴንና አሮንን ተጣሏቸው። እነርሱ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር አመለከቱ። ዘጸ ፭፥፩-፳፫። እግዚአብሔርም ሙሴን ፡- «በጸናች እጅ ይለቅቃቸዋልና፥ በተዘረጋችም ክንድ ከምድሩ አስወጥቶ ይሰድዳቸውልና፥ አሁን በፈርዖን የማደርገውን ታያለህ፤» አለው። በሙሴና በአሮን እጅም እግዚአብሔር ተአምራትን አደረገ። ግብፃውያንንም በአሥር መቅሠፍታት ገረፋቸው። ዘፍ ፯፤፰፤፱፤፲፤፲፩፤
፫፥፱፦ እስራኤል ከግብፅ መውጣታቸው፤
          እግዚአብሔር ለሙሴና ለአሮን ስለ ፋሲካ ነገራቸው። እነርሱም ለሕዝቡ፡- ሁሉም በየቤቱ የፋሲካ ጠቦት እንዲያዘጋጁ፥ ከሚያዝያ አሥር እስከ አሥራ አራት አስረው ካቆዩት በኋላ በሠርክ እንዲያርዱት፥ ከደሙም ወስደው የቤቱን መቃንና ጉበኑን እንዲቀቡት፥ የየቤቱ የሰው ቁጥር ሰባት ወይም አሥር ወይም አሥራ ሁለት እንዲሆን፥ ሥጋውን ከመራራ ቅጠል ጋር የተጠበሰውን እንዲበሉ፥ እለቱን እንዲጨርሱ እንጂ ለነገ ብለው እንዳያሳድሩ፤ ወገቦቻቸውን ታጥቀው፥ ጫማቸውን ተጫምተው፥ በትራቸውን ጨብጠው፥ በችኰላ እንዲበሉ ነግረዋቸዋል።
          ታስሮ የቆየው ጠቦት በአይሁድ እጅ ተይዞ ለታሰረ ለክርስቶስ ምሳሌ ነው። በሠርክ መሠዋቱ፦ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ለመሠዋቱ ምሳሌ ነው። የጠቦቱ ደም የቤቱ ጉበንና መቃን መቀባቱ፦ የክርስቶስ ደም በመስቀል ላይ ለመፍሰሱ ምሳሌ ነው። የየቤቱ የቤተሰብ ቁጥር መወሰኑም ምክንያት አለው። ይኸውም፦ ሰባት ቁጥር በዕብራውያን ፍጹም ቁጥር በመሆኑ ፍጹም እምነትን፥ አሥር ቁጥር ሙሉ ቁጥር በመሆኑ ሙሉ እምነትን፥ አሥራ ሁለት ቁጥር ለጊዜው አሥራ ሁለቱን ነገደ እስራኤል፥ ለፍጻሜው ግን አሥራ ሁለቱን ሐዋርያት ያመለክታል። ሥጋውን በእሳት ጠብሰው መብላታቸው፡- የክርስቶስ ሥጋና ደም እሳተ መለኮት የተዋሀደው ለመሆኑ፥ ከመራራ ቅጠል ጋር መብላታቸው ደግሞ አሥራ ስምንት ሰዓት ጾመን ለአፋችን መረር ሲለን ለመቁረባችን ምሳሌ ነው። ለነገ አታሳድሩ መባላቸው፦ ሥጋውና ደሙ ተሠውቶ፥ ተፈትቶ ላለማደሩ ምሳሌ ነው። ወገብ መታጠቅ ለልብ ንጽሕና፥ ጫማ ለምግባር፥ በትር ደግሞ ለመስቀልና ለእመቤታችን ምሳሌዎች ናቸው። ሕዝቡም የተባሉትን ፈጽመው ከባርነት ቤት ከግብፅ ወጥተዋል። ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ የግብፃውያንን በኵር ሁሉ ሲገድል የጠቦቱን ደም በየበራቸው እያየ እስራኤላውያንን አልፏቸዋል። ይህም በሥጋ ወደሙ የታተሙ ምእመናን መቅሠፍት፥ ሞተ ነፍስ እንደሌለባቸው ምሳሌ ነው። ከግብፅ መውጣታቸውም፡- በኋለኛው ዘመን በክርስቶስ ቤዛነት ነፍሳት ከሲኦል ለመውጣታቸው ምሳሌ ነው። ዘጸ ፲፪፥፩-፶፩።
          የእግዚአብሔር መልአክ ከፊት ከፊታቸው እየሄደ ቀን ቀን በደመና ዓምድ፥ ሌሊት ሌሊት ደግሞ በብርሃን ዓምድ መርቷቸዋል። በሙሴ በትር ኃይለ እግዚአብሔር ተገልጦ ባሕረ ኤርትራን በደረቅ ተሻግረውል፥ ፈርዖንን ግን እስከነ ሠራዊቱ አስጥሞላቸዋል። ይህም በክርስቶስ ቤዛነት ነፍሳት ባሕረ እሳትን ለመሻገራቸው፥ ዲያብሎስና ሠራዊቱ ደግሞ ድል ለመሆናቸው ምሳሌ ነው። ዘጸ፲፫፥፲፯-፳፪፤ ፲፬፥፩-፴፩። በመንገዳቸውም መና ከሰማይ እየወረደ፥ ውኃ ከዐለት እየፈለቀ ተመግበውል። ዘጸ ፲፮፥፩። በሌላ በኵል ደግሞ በደመና ተጋርደው ባሕረ ኤርትራን መሻገራቸው የጥምቀት ምሳሌ ነው። መናውና ውኃው የሥጋውና የደሙ ምሳሌ ነው። ዐለቱ ደግሞ የክርስቶስ ምሳሌ ነው። ይኸንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- «ወንድሞቻችን ሆይ፥ አባቶቻችን ሁሉ ደመና እንደጋረዳቸው ሁሉም በባሕር መካከል አልፈው እንደሄዱ ልታውቁ እወዳለሁ። ሁሉንም ሙሴ በደመናና በባሕር አጠመቃቸው፤ ሁሉም ያን መንፈሳዊ ምግብ ተመገቡ፤ ሁሉም ያን መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ፤ ይኸውም በኋላቸው ከሚሄደው ከመንፈሳዊ ዐለት የጠጡት ነው፤ ያም ዐለት ክርስቶስ ነበረ።» በማለት ተርጉሞልናል። ፩ኛ ቆሮ ፲፥፩። «ከሚከተላቸው ድንጋይ፤» መባሉም ይዘውት ይጓዙ ስለነበረ ነው። ሙሴ በበትር ሲመታው በአሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል ልክ፡- በአሥራ ሁለት በኵል እንደአጋተ የላም ጡት፦ ወተት የመሰለ ውኃ ይወጣው ነበር። ይኸንን የምድረ በዳ ድንጋይ የበረከት ምንጭ ያደረገ አምላክ፡- እመቤታችንን፥ ቅዱሳንን፥ ታቦቱን፥ ሥዕሉን፥ መስቀሉን፥ ሌሎቹንም የበረከት ምንጭ አላደረጋቸውም ማለት አይገባም። እነዚያ ድንጋዩን ተሸክመው፥ አክብረው፥እንደተጓዙ፦ እኛም ጌታ የሰጠንን የበረከት ምንጮቻችንን ሁሉ ተሸክመን፥አክብረን እንጓዛለን፥ እንኖራለን።
፫፥፲፦ ሙሴና የእግዚአብሔር ክብር፤
          እግዚአብሔር በመንገዱ ሁሉ፡- «እኔ በፊትህ እሄዳለሁ፥ አሳርፍህማለሁ፤ . . . ይህን ያልኸኝን ነገር አደርግልሃለሁ፤ በፊቴ ሞገስን አግኝተሃልና ከሁሉ ይልቅ አውቄሃለሁና፤  . . .  እኔ በክብሬ በፊትህ አልፋለሁ . . .  እጄን በላይህ እጋርዳለሁ።» ይለው ነበር። በደብረ ሲና የሰጠው ጽላት ተሰብረውበት ስለ ነበር፡- ፈቅዶለት እንደገና ሠርቶ አስባርኳል። ፊቱም እንደ ፀሐይ አብርቷል። ዘጸ ፴፫፥፲፪፤፴፬፥፩። በዚህም እግዚአብሔር ክብሩን ለሙሴ አሳይቷል፥ ክብሩን በሙሴ ላይ ገልጧል። በአጠቃላይ አነጋገር፡- የክብሩ መገለጫ፥ የበረከቱ መስጫ አድርጐታል። እንኳን እርሱን በትሩን እንኳ የኃይሉ መገለጫ አርጐታል። ታቦቱ ያለበትን የመገናኛውን ድንኳንም የእግዚአብሔር ክብር ተለይቶት አያውቅም። «ድንኳኑና በምሥዋዑ ዙሪያ የቅጽሩን ዓምዶች አቁሞ መጋረጃውን ጋረደ፤ የቅጽሩንም በር እግዚአብሔር እንዳዘዘው አድርጎ ጋረደው። ሙሴም እንዲህ አድርጎ ሥራውን ሁሉ ሠርቶ ጨረሰ፥ ድንኳኒቱንም ብሩህ ደመና ሸፈናት፥ የእግዚአብሔርም ብርሃን ሰፍሮባት ታየ። ሙሴም ወደ ደብተራ መግባት ተሳነው። ደመናው ከድንኳኒቱ ላይ ከተነሣ በኋላ ግን የእስራኤል ልጆች በየነገዳቸው ይጓዙ ነበር። (ነገደ ቢኒያም ሁለቱን ነገድ ይዘው በፊት ይጓዛሉ፥ ቀጥለው ነገደ ሮቤል ሁለቱን ነገድ ይዘው ይጓዛሉ፥ ሌዋውያን ካህናትም ታቦትንና ንዋየ ቅዱሳቱን ይዘው በመካከል ይጓዛሉ፥ ከዚያ ቀጥለው ነገደ ምናሴ ሁለቱን ነገድ ይዘው ይጓዛሉ)። ደመናው ከድንኳኑ ካልተነሣ አይጓዙም ነበር፤ ምክንያቱም አለመነሣቱ አትጓዙ ሲል ነውና። ተጉዘው በሚሰፍሩበት ሁሉ ደመናው እስራኤል እያዩት ቀን በድንኳኑ ላይ ሰፍሮ ይውልና ሌሊት ዓምደ እሳት ሁኖ ሲያበራላቸው ያድር ነበር።» ይላል። ይህም የአዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያን በእግዚአብሔር ክብር ለመመላቷ፥ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ለመሆኗ ምሳሌ ነው።
፫፥፲፩፦ አሮንና ማርያም፤
          ሙሴ የኢትጵያን ሴት አግብቶ ነበርና፡- «እኛን ከአረማውያን አትጋቡ እያለን እርሱ ግን ያገባል፤» እያሉ ወንድሙ አሮንና እኅቱ ማርያም አሙት። «በውኑ እግዚአብሔር ሙሴን ብቻ ተናገረውን? እኛንስ የተናገረን አይደለምን?» ተባባሉ። ሙሴ ግን በዚህ ዓለም ካለው ሰው ይልቅ ፈጽሞ ደግ ሰው ነበር። እግዚአብሔርም፡- ሙሴንና አሮንን ማርያምንም፡- «ሦስታችሁም ፈጥናችሁ ወደ ደብተራ ኦሪት ኑ፤» አላቸው እነርሱም ፈጥነው ሄዱ። እግዚአብሔርም በዓምደ ብርሃን ወደ ደብተራ ኦሪት ወርዶ አሮንን እና ማርያምን ስለጠራቸው ሁለቱም ቀረብ አሉ። እርሱም፡- «ነገሬን ስሙ፥ ከእናንተ ለእግዚአብሔር ነቢይ የሆነ ሰው ቢኖር በራእይ እገጽለታለሁ፥ በሕልምም እነጋገረዋለሁ። ነገር ግን የምናገረው እነደታመነ ወዳጄ እንደ ሙሴ አይደለም፤ እሱ በወገኖቼ በእስራኤል ሁሉ የታመነ ነውና፤ ተገልጬ ቃል በቃል እነጋገረዋለሁ እንጂ በራእይ ወይም በሕልም የምነጋገረው አይደለም፥ የእግዚአብሔርነቴን ጌትነትም ያየ እሱ ነው። ወዳጄ ሙሴን ማማትን ለምን አልፈራችሁም?» አላቸው፤ ተቆጥቶባቸውም ሄደ። (እግዚአብሔር ፈርዶ ያመጣው መከራ በእነርሱ ላይ ተደረገ)።
፫፥፲፪፦ አሮን ወደ ሙሴ፤ . . .  ሙሴ ወደ እግዚአብሔር፤
          ደመናውም ከደብተራ ኦሪት ተወገደ፤ (ራቀ)፤ ማርያምን ወዲያው ለምጽ ያዛት፥ ሁለንተናዋም እንደ በረዶ ነጭ ሆነ። አሮንም ወደ ማርያም ተመልሶ ቢያይ ለምጽ ይዟት ቢያገኛት አዘነ፥ ደነገጠ። ሙሴንም፡- «ጌታዬ ሆይ፥ እባክህ እሺ በጄ በለኝ፥ እንደበደልን አላወቅንምና በእኛ ዕዳ አታድርግብን፤ ከእናት ማኅፀን እንደወጣ ጭንጋፍ፡- በሞት የተለቀምን አንሁን፤» አለው። ወንድሟን አምታለችና የማርያም የሰውነቷ እኵሌታ በለምጽ ነደደ። ሙሴም፡- «አቤቱ፥ እሺ በጀ በለኝና ማርያምን ከለምጽ አድናት፤» ብሎ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ። እግዚአብሔርም ሙሴን፡- «አባቷ ምራቁን በፊቷ ቢተፋባት እንኳ ሰባት ቀን ታፍር ዘንድ ይገባት ነበር፤ ሰባት ቀን ከሰፈር ውጭ ተዘግታ ትቀመጥ፤ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈር ትመለስ፤» አለው። ማርያምም ከሰፈር ወጥታ ሰባት ቀን ተቀመጠች። ሕዝቡም እርሷ እስክትነጻ ድረስ አልተጓዙም። ዘኁ ፲፪፥፩-፲፭። በዚህም እነ አሮን በጸጋ የከበረ ሙሴን «ጌታ» ብለው እንደጠሩት እናስተውላለን።

7 comments:

 1. ቃለህይወት ያሰማልን ያገልግሎት ጊዜዎን ይባርክለዎት
  (እባከወትን ስርዓተ ቤተክርስትያን የሚል አምድም ጨምሩ ገ/ስላሴ ነኝ ከህንድ)

  ReplyDelete
 2. ቃለህይወት ያሰማልን

  ReplyDelete
 3. #ከሚያየው ይልቅ የማይታየውን ሊፈራ ወዷልና$
  #በመንፈሳዊውም ሆነ በሥጋዊው ዓለም ከላይ እስከታች ለሥልጣን ብለን ለምንጋደል ሰዎች ይህ የሙሴ ሕይወት ለእኛ ታላቅ ተግሣፅ ነው$
  እግዚሀብሔር ይስጥልን …… ይህን ሚስጥር አዘል ፅሁፍ እግዚሐብሔር በእርስዎ ላይ አድሮ ስላፃፈዎት እግዚሐብሔር ይመስገን፡፡
  ለእኛም ለምናነበው እንደ ሰለሞን ማስተዋልና ጥበቡን ሰጥቶን ያነበብነውን ለህይወት ያድርግልን
  ላሜዳ ከ አ.አ

  ReplyDelete
 4. ቃለህይወት ያሰማልን

  ReplyDelete
 5. ቃለ ሂወት ያሰማልን.ስርአተ ቤተክርስተያን የሚል አምድ ቢጨመር የሚለው የምደግፈው ሀሳብነው.

  ReplyDelete
 6. ቃለ ሂወት ያሰማልን.ስርአተ ቤተክርስተያን የሚል አምድ ቢጨመር የሚለው የምደግፈው ሀሳብነው.

  ReplyDelete