Sunday, December 5, 2010

ነገረ ቅዱሳን ክፍል፡- ፮

እግዚአብሔርን መምሰል፡- (በጸጋ በመክበር፤)
          እግዚአብሔርን የሚመስለው ማለትም የሚተካከለው እንደሌለ ቅዱሳት መጻሕፍት በመተባበር ይመሰክራሉ። እግዚአብሔርን በባህርይ የሚመስለው፥ በሥልጣን የሚተካከለው የለምና። በመሆኑም ቅዱሳን በጸጋ ከብረው እርሱን መሰሉት ማለት ተካከሉት (ተስተካከሉት) ማለት አይደለም። ለምሳሌ፡- አዳም በሥላሴ መልክና አርአያ በመፈጠሩ፡- ሥላሴን ተካክሎ ተፈጠረ፥ አያሰኝም። ምክንያቱም በምንም መንገድ ቢሆን ፍጡር ፈጣሪን ሊተካከለው አይችልምና ነው። ነቢዩ ኢሳይያስ፡- «እንግዲህ እተካከለው ዘንድ በማን መሰላችሁኝ? ይላል ቅዱሱ፤» በማለት የተናገረው ለዚህ ነው። ኢሳ ፵፥፳፭።
          በጸጋ እግዚአብሔር የከበሩ ቅዱሳን በብዙ ነገር የጠራቸውን እግዚአብሔርን መስለውታል። ይኸውም ራሳቸውን በመካዳቸው (ፈቃደ ሥጋቸውን ለፈቃደ ነፍሳቸው) በማስገዛታቸው ነው። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡- «እኔን መከተል የሚወድ (ሊመስለኝ የሚፈቅድ) ቢኖር ራሱን ይካድ፤» ያለው ለዚህ ነውና። ማቴ ፲፮፥፳፬። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- በዚህ ቃለ ምክር ዘክርስቶስ በመጓዙ፡- «እኔ ክርስቶስን መስያለሁ፤» ለማለት በቅቷል። ፩ኛ ቆሮ ፲፩፥፩። በሮሜ መልእክቱም፡- «እግዚአብሔር የሚወዱትን ምርጦቹን በበጎ ምግባር ሁሉ እንደሚረዳቸው እናውቃለን። ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኲር ይሆን ዘንድ (ለቅዱሳን ለበጎ ምግባር ሁሉ አብነት ይሆናቸው ዘንድ) አስቀድሞ ያወቃቸውንና የመረጣቸውን እነርሱን ልጁን (ኢየሱስ ክርስቶስን) ይመስሉ ዘንድ አዘጋጅቷቸዋል። ያዘጋጃቸውን እነርሱን ጠራ፥ የጠራቸውንም እነርሱን አጸደቀ፥  ያጸደቃቸውንም እነርሱን አከበረ፤» ብሏል። ሮሜ ፰፥፳፰። ለፊልጵስዩስ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ደግሞ፡- «እርሱም እንደ ከሃሊነቱ ረዳትነት መጠን የተዋረደውን ሥጋችንን የሚያድሰው፥ ክቡር ሥጋውንም እንዲመስል የሚያደርገው፥ የሚያስመስለውም፥ ሁሉም የሚገዛለት (የሁሉ ገዥ) ነው።» ብሏል።
ወልድ (የባህርይ ልጅ)፤
          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአብ ልጅ፥ የማርያም ልጅ ነው። «እግዚአብሔር አለኝ፥ አንተ ልጄ ነህ፥ እኔም ዛሬ ወለድሁህ፤» እንዲል፡- ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት ተወልዷል። መዝ ፪፥፯። ይኸንንም በዮርዳኖስና በደብረ ታቦር፡- «በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወድደው ልጄ ይህ ነው፤» በማለት የባህርይ አባቱ አብ መስክሮለታል። ማቴ ፫፥፲፯፣ ፲፯፥፭። እርሱም አባቴ እያለ ለባህርይ አባቱ ለአብ መስክሮለታል። ዮሐ ፲፩፥፵፩፣ ፲፬፥፪፣፳። በመሆኑም ተቀዳሚና ተከታይ የሌለው የአብ የባህርይ ልጅ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ፡- «የእግዚአብሔር ልጅ እንደመጣ፥ እውነተኛም የሆነውን እናውቅ ዘንድ ልቡናን እንደሰጠን እናውቃለን፤ እውነተኛም በሆነው በእርሱ አለን፥ እርሱም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።» ያለው ለዚህ ነው። ፩ኛ ዮሐ ፭፥፳። «መንፈስ ቅዱስ ያድርብሻል፥ የልዑል ኃይልም ይጋርድሻል፥ ከአንቺ የሚወለደውም ቅዱስ ነው፤ የልዑል እግዚአብሔር ልጅም ይባላል።»  እንዲል በመንፈስ ቅዱስ ግብር ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም፡- ያለ አባት ተወልዷል። ሉቃ ፩፥፴፭፤፪፥፮። ይኸንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- «ነገር ግን ቀጠሮው በደረሰ ጊዜ፥ (አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም)፥ እግዚአብሔር ልጁን(አብ ወልድን)ላከ፤ ከሴትም (ከሴቶች ሁሉ ተለይታ ከተባረከችው ከድንግል ማርያም) ተወለደ።» በማለት መስክሯል። ገላ ፬፥፬። በመሆኑም ከሁለት አካል አንድ አካል፥ ከሁለት ባህርይ አንድ ባህርይ (በተዋህዶ አንድ አካል አንድ ባህርይ) የሆነውን ኢየሱሰ ክርስቶስን የባህርይ አባቱ አብ «ልጄ» እንዳለው ሁሉ እመቤታችንም «ልጄ» ብላዋለች። ሉቃ ፪፥፵፰።
ውሉድ (የጸጋ ልጆች)፤
          ቅዱሳን ልጅነታቸውን አጽንተው የጠበቁ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው። ይኸንንም ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ፡- «ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑ የእግዚአብሔር ልጆች እንዲሆኑ ሥልጣንን ሰጣቸው። እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከሥጋዊና ከደማዊ ግብር ወይም ከወንድና ከሴት ፈቃድ አልተወለዱም።» በማለት ተናግሮታል። ዮሐ ፩፥፲፪። ከሁሉም በላይ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡- «እናንተስ በምትጸልዩበት ጊዜ፡- አባታችን ሆይ፥ በሰማያት የምትኖር፥ ስምህ ይቀደስ፥ በሉ።» ያለው ለዚህ ነው። ማቴ ፮፥፱። በተጨማሪም «ለሰዎች በደላቸውን ይቅር ብትሉ፥ ሰማያዊው አባታችሁ ይቅር ይላችኋልና። ነገር ግን ለሰዎች በደላቸውን ይቅር ባትሉ አባታችሁም በደላችሁን የቅር አይላችሁም።» በማለት የእግዚአብሔር ልጆች መሆናቸውን ለደቀመዛሙርቱ አረጋግጦላቸዋል። ማቴ፮፥፲፬። በእርግጥ በአብ፥ በወልድ፥ በመንፈስ ቅዱስ ስም ተጠምቀን ሁላችንም የእግዚአብሔር ልጆች ሆነናል። ማቴ፳፰፥፲፱፣ ዮሐ ፫፥፫፤ ነገር ግን፡- «ኃጢአትን የሚሠራትም ከሰይጣን ወገን ነው፥ ጥንቱን ሰይጣን በድሏልና፤ ስለዚህ የሰይጣንን ሥራ ይሽር ዘንድ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ። ከእግዚአብሔር የሚወለድ ሁሉ ኃጢአትን አይሠራም፤ ዘሩ በእርሱ ይኖራልና፤ ኃጢአትንም ሊሠራ አይችልም፤ ከእግዚአብሔር ተወልዷልና። በዚህም የእግዚአብሔር ልጆችና የሰይጣን ልጆች ይታወቃሉ፤ ጽድቅንም የማይሠራ ሁሉ ከእግዚአብሔር የተወለደ አይደለም፤ ወንድሙንም የማይወድ እንዲሁ ነው።» የሚለውን ለመፈጸም እንቸገራለን። ፩ኛ ዮሐ ፫፥፭።
          አካላው ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ቢባል የባህርይ ነው። ይህም ማለት፦ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው የአብ የባህርይ ልጅ ነው፥ማለት ነው። በመሆኑም፦ አብ አባት በመሆን ወልድን አይበልጠውም፥ አይቀድመውም። ጌታችን በወንጌል፦ «እኔና አብ አንድ ነን፤» እንዳለ፥ በመለኰት፥ በባህርይ፥ በሥልጣን፥ በፈቃድ አንድ ናቸው። ዮሐ ፲፥፴። በተጨማሪም «እኔ በአብ እንዳለሁ፥ አብም በእኔ እንዳለ እመኑ፤ ያለዚያም ስለ ሥራዬ እመኑኝ።» እንዳለ በህልውና አንድ ናቸው። ዮሐ ፲፬፥፲፩። የቅዱሳን «የእግዚአብሔር ልጆች» መባል ግን የጸጋ ነው። በመሆኑም በጸጋ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው፡- «የእግዚአብሔር ልጅ» የተባለ ኢየሱስ ክርስቶስን መስለውታል። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤው ዕለት፥ ለመግደላዊት ማርያም በተገለጠላት ጊዜ፡- «ወደ አባቴ፥ ወደ አባታችሁ--- አርጋለሁ፤ ብሏል፥ ብለሽ ለደቀመዛሙርቴ ንገሪ፤» ያላት ለዚህ ነው። ምክንያቱም «ወደ አባቴ» ማለቱ እርሱ ለአብ የባህርይ ልጅ በመሆኑ ነው።  «ወደ አባታችሁ» ማለቱ ደግሞ እነርሱ የጸጋ ለጆች በመሆናቸው ነው። እንደዚያ ባይሆን ኖሮ፡- ጠቅለል አድርጎ «ወደ አባታችን» ባለ ነበር። ዮሐ ፳፥፲፯።

የባህርይ አምላክ፤
          አምላክ፥ ማለት፥ ፈጣሪ፥ ገዥ፥ ፈራጅ፥ ዳኛ፥ ሠሪ፥ ቀጭ፥ ፈላጭ ቆራጭ ማለት ነው። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡- የፈጠረውን ፍጥረት የሚገዛ የባህርይ አምላክ ነው። ይህም ገዥነት የባህርይ ገንዘቡ የሆነ ማለት ነው። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ፡- «በመጀመሪያ ቃል (ወልድ) ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ (በአብ ህልው ሆኖ፥ ከአብ ተካክሎ፥ በዘመን ሳይቀዳደሙ፥ በሥልጣን ሳይበላለጡ፥ በቅድምና) ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። (ፈጥሮ የሚገዛ ነው)፤  ይህም በመጀመሪያ በእግዚአብሔር ዘንድ (በመንፈስ ቅዱስ ህልው ሆኖ፥ ከመንፈስ ቅዱስ ተካክሎ፥ በዘመን ሳይቀዳደሙ፥ በሥልጣን ሳይበላለጡ፥ በቅድምና) ነበረ። ሁሉም በእርሱ ሆነ፤ (የሚታየውም የማይታየውም፥ የሚያልፈውም የማያልፈውም ሁሉም በእርሱ አምላክነት ተፈጠረ)፤ ከሆነውም ሁሉ ያለ እርሱ ምንም የሆነ የለም። (እርሱ ሳይኖር፥ ያለ እርሱ አምላክነት የተፈጠረ ፍጥረት የለም)» ያለው ለዚህ ነው። ዮሐ ፩፥፩። በመልእክቱም ላይ፡- «እርሱም እውነተኛ አምላክና የዘለዓለም ሕይወት ነው፤» ብሏል። ፩ኛ ዮሐ ፭፥፳። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፡- «ከእነርሱም (ከቤተ አይሁድ) ክርስቶስ በሥጋ መጣ፤ (ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ በተዋህዶ ሰው ሁኖ ተወለደ)፤ እርሱም ከሁሉ በላይ ሁኖ (የፈጠረውን ፍጥረት እየገዛ) ለዘለዓለም የተባረከ (የተመሰገነ) አምላክ ነው፤» ብሏል። ሮሜ ፱፥፭።
የጸጋ አማልክት፤
          ቅዱሳን የጸጋ ገዢዎች ናቸው። ጸጋ ማለት፡- ሀብት፥ መልካም ስጦታ፥ ዕድል ፈንታ፥ ትምርት፥ ስርየት፥ ይቅርታ፥ብዕል፥ ክብር፥ ሞገስ፥ የቸርነት ሥራ፥ ያለዋጋ የሚሰጥና የሚደረግ ማለት ነው። እንደሚታወቀው፥ አባታችን አዳም የተፈጠረው የጸጋ አምላክ (ገዥ) ሁኖ ነው። ይኸውም፡- «እግዚአብሔርም አለ፡- ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ፤» በሚለው የእግዚአብሔር ቃል ታውቋል። ዘፍ ፩፥፳፮። እርሱም እንደ ገዥነቱ ለእያንዳንዳቸው ስም አውጥቶላቸዋል። ወደ ገዢያቸው ወደ አዳም ሰብስቦ ያመጣቸውም እግዚአብሔር ነበር። ዘፍ ፪፥፲፱።
          እግዚአብሔር በግብፅ ሀገር ለወዳጁ ለሙሴ በተገለጠለት ጊዜ፡-«እነሆ፥ እኔ ለፈርዖን  አምላክ አድርጌሃለሁ፤ ወንድምህም አሮን ነቢይ ይሆንልሃል።» ብሎታል። ዘዳ ፯፥፩። ይህም በእርሱ ላይ አሰለጥንሃለሁ ሲለው ነው። አንድም፦ አምላክ የወደደውን እንደሚያደርግ ሁሉ አንተም የወደድከውን አድርገው ሲለው ነው። በመሆኑም ሙሴ የጸጋ አምላክነቱን (ገዥነቱን) በግብፃውያን ላይ በወረደ አሥር መቅሰፍት አረጋግጧል። እነዚህም፡- የግብፅ ውኃ ወደ ደምነት ተለውጧል፥ የግብፅ ምድር በጓንጉቸሮች ተሸፍኗል፥ በሰውም በእንሰሳም ላይ ቅማል ፈልቷል፥ ተናካሽ ዝንቦች ወርረዋቸዋል፥ የቤት እንሰሳት አልቀዋል፥ ሻህኝ ቁስል ወጥቶባቸዋል፥ ኃይለኛ በረዶ ወርዶባቸዋል፥ የአንበጣ መንጋ ታዝዞባቸዋል፥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ጨለማ ሆኗል፥ ከንጉሡ ጀምሮ የሕዝቡም የበኲር ልጆቻቸው የእንስሳቱም ሳይቀር ሞተውባቸዋል፤
          ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ ለቅዱሳን ስለተሰጠ የጸጋ አምላክነት ሲናገር፡- «እኔ ግን እላለሁ፥ አማልክት ናችሁ፥ ሁላችሁ የልዑል ልጆች ናችሁ፤» ብሏል። መዝ ፹፩፥፮። ጌታችን በወንጌል ይኽንን ጠቅሶ አስተምሯል። «ዳግመኛም አይሁድ ሊወግሩት ድንጋይ አነሡ። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፡- ከአባቴ ብዙ መልካም ሥራ አሳያኋችሁ፤ ከእነርሱ በየትኛው ሥራ ምክንያት ተወግሩኛላችሁ አላቸው። አይሁድም፡- አንተ ሰው ስትሆን ራስህን እግዚአብሔር ታደርጋለህና፥ ስለ መሳደብህ ነው እንጂ ስለ መልካም ሥራህስ አንወግርህም አሉት። ጌታችንም ኢየሱስ መልሶ፡- እኔ አማልክት ናችሁ አልሁ፥ ተብሎ በኦሪታችሁ ተጽፎ የለምን? የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን እነዚያን አማልክት ካላቸው፥ የመጽሐፉ ቃል ይታበል ዘንድ አይቻልም። እኔ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ብላችሁ፥ አብ የቀደሰውንና ወደ ዓለምም የላከውን እንዴት ትሳደባለህ ትሉኛላችሁ? የአባቴን ሥራ ባልሠራ (አምላክ ብቻ ሊሠራው የሚችለውን ሥራ ባላደርግ) በእኔ አትመኑ። ከሠራሁ ግን፥ እኔን እንኳን ባታምኑ እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ ታውቁና ትረዱ ዘንድ ሥራዬን እመኑ፤» ብሏቸዋል። ዮሐ ፲፥፴፩። ቅዱስ ዳዊት፡- «የአማልክት አምላክ እግዚአብሔር ተናገረ፥ ምድርንም ጠራት፤» በማለት የተናገረውም ቅዱሳን በጸጋ አማልክት በመሆናቸው ነው። መዝ ፵፱፥፩።
የባህርይ ንጉሥ፤
          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ ንጉሥ ነው። ቅድመ ዓለም፥ ማዕከለ ዓለም፥ ድኅረ ዓለም ንጉሥ ነው። ቅዱስ ዳዊት፡- «ንጉሤና አምላኬ ሆይ፥ አቤቱ ወደ አንተ እጸልያለሁና፤» እያለ ይማጸነው ነበር። መዝ ፭፥፪። ዘለዓለማዊነቱንም፡- «እግዚአብሔር ለዘላለም ይነግሣል፤» በማለት መስክሯል። መዝ ፱፥፴፮። በማዕከለ ምድር በቀራንዮ፥ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ ዓለምን እንደሚያድን ሲናገርም፡- «እግዚአብሔር ግን ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነው፥ በምድርም መካከል መድኃኒትን አደረገ፤» ብሏል።መዝ ፸፫፥፲፪። ክብር ምስጋና የሚገባው ንጉሥ መሆኑንም፡- «እግዚአብሔር ነገሠ፥ ክብርንም ለበሰ፤» በማለት ተናግሯል። መዝ ፺፪፥፩ ። ከዚህም ሌላ፡- «እናንት መኳንንቶች፥ በሮችን ክፈቱ፥ የዘለዓለም ደጆችም ይከፈቱ፥ የክብርም ንጉሥ ይግባ። ይህ የክብር ንጉሥ ማነው? እግዚአብሔር ነው፥ ብርቱና ኃያል፥ እግዚአብሔር ነው፥ በሰይፍ ኃያል። እናነት መኳንንቶች፥ በሮችን ክፈቱ፥ የዘለዓለም ደጆችም ይከፈቱ፥ የክብርም ንጉሥ ይግባ። ይህ የክብር ንጉሥ ማነው? የጭፍሮች አምላክ እግዚአብሔር፥ እርሱ የክብር ንጉሥ ነው።» የሚል አለ። መዝ ፳፫፥፯። ነቢዩ ኢሳይያስም፡- «እነሆ ጻድቅ ንጉሥ ይነግሣል፤ --- ንጉሥን በክብሩ ታዩታላችሁ፤» ያለው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ኢሳ ፴፪፥፩፣ ፴፫፥፲፯። ጊዜውም ሲደርስ የባህርይ ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ በክብር ዙፋኑ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ላይ ነግሦአል፥ ተገልጧል። ነቢዩ ኤርምያስ ደግሞ፡- «እነሆ ለዳዊት የጽድቅ ቁጥቋጥ የማስነሣበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እንደ ንጉሥ ይነግሣል፥ ይከናወንለታልም፥ በምድርም ፍርድንና ጽድቅን ያደርጋል፤» ብሏል። ኤር ፳፫፥፭። ይኽንን ትንቢት ሲጠባበቁ የኖሩ ሰዎችም፡-ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አያነጠፉ፥ የዛፍ ቅርንጫፎችን እየጐዘጐዙ፥ ዘንባባ ይዘው፥ ሆሣዕና የዳዊት ልጅ፥ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው፥ ሆሣዕና በአርያም፤» እያሉ ተቀብለውታል። ማቴ ፳፩፥፰። መንግሥቱም የምታልፍ፥ የምትጠፋ፥ ምድራዊት ሳትሆን፥ የማታልፍ፥ የማትጠፋ ሰማያዊት ናት። ይኸንንም «የእኔ መንግሥት ከዚህ አይደለችም፤ መንግሥቴስ በዚህ ዓለም ብትሆን ኖሮ ለአይሁድ እንዳልሰጥ አሽከሮቼ (መላእክት) በተዋጉልኝ ነበር፤ አሁንም መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም፤» በማለት ለጲላጦስ ነግሮታል። ዮሐ ፲፰፥፴፮። ይኸንን በተመለከተ፡- ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ፡- «እንዲሁ ወደ ዘለዓለሙ ወደ ጌታችንና መድኃኒታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት መግባት በምልዐት ይሰጣችኋል፤» ብሏል፤ ፪ኛ ጴጥ ፩፥፲፩።
ነገሥታት ዘበጸጋ
          ቅዱሳን የጸጋ ነገሥታት ናቸው። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «የነገሥታት ንጉሥ፤» ተብሎ የተጠራው በእነርሱ ላይ ነው። የኸንንም ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ፡- «የነገሥታት ንጉሥ--- የሚል ስም አለው፤» በማለት በራእይ መጽሐፉ ነግሮናል፡ ራእ ፲፱፥፲፮። በወንጌል እንደተጻፈ ጌታችን ደቀመዛሙርቱን፡- «በአሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ፤» ማለቱም የሚያመለክተው በጸጋ ነገሥታት መሆናቸውን ነው። ምክንያቱም በዙፋን የሚቀመጥ ንጉሥ ነውና። ማቴ ፲፱፥፳፰። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በበኩሉ፡- «ይልቁን የጸጋን ብዛትና የጽድቅን ስጦታ ብዛት የሚቀበሉ በአንዱ በኢየሱስ ክርስቶስ በኲል በሕይወት ይነግሣሉ፤» ብሏል። ሮሜ ፭፥፲፯። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ደግሞ «ከዚህም በኋላ ዙፋኖች ተዘርግተው፥ የሰው ልጅም (በተዋህዶ ሰው የሆነው አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ) በላያቸው ተቀምጦ አየሁ፤ ስለ ኢየሱስ ምስክርና (በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ስላመኑ፥ ስሙን ስላስተማሩ፥ በስሙ ስለተጠሩ) ስለ እግዚአብሔር ቃልም (በአካላዊ ቃል በኢየሱስ ክርስቶስ ስላመኑ አንድም ቃሉን ስላስተማሩ) ለተገደሉት ነፍሳት ቅን ፍርድ ተፈረደላቸው፤ ለአውሬውና ለምስሉም ያልሰገዱትን፥ በግምባራቸውና በእጃቸው ላይ ምልክቱን ያልጻፉትንም አየሁ፥ እነርሱም ከክርስቶስ ጋር ሺህ ዓመት ኖረው (የዘለዓለም ሕይወት ባለቤት ሆነው) ይነግሣሉ።» ብሏል። ራእ ፳፥፬። በመሆኑም የባህርይ ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱሳንን በጸጋ ነገሥታት አድርጎ ራሱን አስመስሏቸዋል።

ክፍል ፯

7 comments:

 1. MEMIHIR KISIS DEGENE AMLAKE KIDUSAN YITEBIKILIN
  K H Y

  ReplyDelete
 2. qale hiwot yasemalin

  ReplyDelete
 3. ቃለ ህይወትን ያሰማልን፡መንግስተ ሰማያትን ያውርስልን አባታችን፡፡

  ReplyDelete
 4. Kale hiyewet Yasemalen

  ReplyDelete
 5. Kale heyewet yasemalen

  ReplyDelete
 6. Weldelibanos AbereheDecember 6, 2011 at 12:08 PM

  melake selam Kale heyewet yasemalen

  ReplyDelete
 7. melake selam Kale heyewet yasemalen

  ReplyDelete