Sunday, November 28, 2010

ነገረ ቅዱሳን ክፍል ፭፤

                                   እግዚአብሔርን፤ መምሰል፤ (በተፈጥሮ)፤

«ወይቤ እግዚአብሔር ንግበር ስብአ በአርአያነ ወበአምሳሊነ፤ እግዚአብሔር፦ ዓርብ በነግህ ፥ በእኛ አምሳል፥ በእኛ አርአያ ሰውን እንፍጠር አለ፤» እንዲል፦ የሰው ልጅ የተፈጠረው በእግዚአብሔር አርአያ፥ በእግዚአብሔር አምሳል ነው፤ ይህም ታላቅ ቅድስና ነው። «እግዚአብሔርም አለ፤» የሚለው፦ ሥላሴ፦ በመለኰት፥ በሥልጣን፥ በባህርይ፥ በፈቃድ፥ በህልውና አንድ መሆናቸውን ያስገነዝበናል። «በመልካችን፥ በምሳሌያችን እንፍጠር፤» የሚለው ደግሞ የስም፥ የአካል፥ የግብር ሦስትነታቸውን ያስተምረናል። ሥላሴ አንድም ሦስትም ናቸውና። አንድነታቸው ሦስትነታቸውን አይጠቀልለውም፥ ሦስትነታቸውም አንድ መሆናቸውን አያጠፋውም። «ምሥጢረ ሥላሴ፤» እንዲል፦ የሥላሴን ነገር ምሥጢር የሚያሰኘው ይህ ነው። ዘፍ ፩፥፳፮። በአንድነት በሦስትነት የሚመሰገኑ ሥላሴ አዳምን፦

፩-፩ አዋቂ አድርገው ፈጥረውታል፤

            እግዚአብሔር አዳምን በነግህ የፈጠረው፥ የንጋት  (የማለዳ) ተከታይ ብርሃን ስለሆነ ነው። ብርሃን የዕውቀት ምሳሌ ሲሆን ጨለማ ደግሞ የድንቊርና ምሳሌ ነው። ይህም የሚያመለክተው ልበ ብርሃን (አዋቂ) አድርጐ እንደፈጠረው ነው። አባታችን አዳም እናታችን ሔዋን ከጐኑ ስትፈጠር ማዕከለ ንቃሕ ወንዋም (በመንቃትና በማንቀላፋት መካከል) ነበር። ይህም፦ ፈጽሞ አልነቃም ፈጽሞም አልተኛም ማለት ነው። በመሆኑም የተሰማውም የታየውም ነገር የለም። ነገር ግን፥ ሔዋን ከወዴት እንደመጣች አውቆ፦ «ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት፥ ሥጋም ከሥጋዬ ናት፥ እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል።» ብሏል። ዘፍ ፪፥፳፫። «ሕዝብ ዚይነብር ውስተ ጽልመት፥ ርእየ ብርሃነ ዓቢየ፤ በጨለማ ላሉ ሕዝብ ታላቅ ብርሃን ወጣላቸው፤ (በድንቊርና፥ በቀቢጸ ተስፋ፥ ለነበሩ ሰዎች ዕውቀት ተሰጣቸው)፤» የሚለው ኃይለ ቃልም የሚያስተምረን ብርሃን የዕውቀት ምሳሌ መሆኑን ነው። ኢሳ ፱፥፩፣ ማቴ ፬፥፲፬። ጻድቁ ካህን ዘካርያስም፦ «ይህም ከላይ የመጣ ብርሃን በጐበኘበት በአምላካችን ምሕረትና ርኅራኄ ምክንያት ነው፤ ብርሃኑም በጨለማና በሞት ጥላ ተቀምጠው ላሉት ያበራል፤» ብሏል። ሉቃ ፩፥፸፰ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ «በጨለማ ውስጥ ብርሃን ይብራ፤ ያለ እግዚአብሔር፦ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት የክብሩን ዕውቀት በልባችን አብርቶልናልና፤» ብሏል ፪ኛ ቆሮ ፬፥፱።

፩፥፪ የጸጋ አምላክ ፣ ንጉሥ አድርገው ፈጥረውታል

            አምላክ ማለት ገዥ ማለት ነው፤ አምላክነት የባህርይ ገንዘቡ የሆነ፥ የፈጠረውን ፍጥረት የሚገዛ እግዚአብሔር ብቻ ነው። «የጸጋ» ማለት ግን «የሥጦታ» ማለት ነው። «የባሕር ዓሣዎችንና የምድር አራዊትን የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ በምድርም ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሁሉ ይግዛ፤» እንዲል፦ ለአዳም ከሰማይ በታች ያለውን ፍጥረት ሁሉ እንዲገዛ ሥልጣን ሰጥቶታል ዘፍ ፪፥፳፮። አዳምም እንደ ገዥነቱ ለሰማይ አዕዋፋት ለምድር እንስሳትና ለዱር አራዊት ሁሉ ስም አውጥቶላቸዋል። ዘፍ ፪፥፲፱። እግዚአብሔር ባወቀ ይሰግዱለትም ነበር። እንኳን እርሱ ፀሐይ እንኳ የተፈጠረው ቀንን እንዲገዛ ነው፥ ጨረቃና ከዋክብት ደግሞ ሌሊትን እንዲገዙ ነው። መዝ ፻፴፭፥፰።

            አዳም ከእግዚአብሔር ከተጣላ በኋላ የማይታዘዙት ሆነው ነው እንጂ ከዚያ በፊት ፍጥረታት ሁሉ ይታዘዙለት ይገዙለት ነበር። ይህ ጸጋ በቅዱሳን ሕይወት ላይ ታይቷል። ለጻድቁ ለኖኅ እንስሳቱ፥ አራዊቱ፥ አዕዋፋቱ፥ ሁሉም፦ «እሺ በጀ፤» ብለው ወደ መርከብ ገብተውለታል። ዘፍ ፮፥፳። ለሊቀ ነቢያት ለሙሴ ባሕረ ኤርትራ ታዝዛለታለች። ዘጸ ፲፬፥፳፩ ለኢያሱ ወልደ ነዌ ፀሐይና ጨረቃ ተገዝተውለታል፤ ፀሐይ ሰዓቷን ጠብቃ የማትጠልቅ ሆነች፥ ጨረቃም ዘገየች። ኢያ ፲፥፲፪። ለነቢዩ ለኤልያስም ሰማይ ስለተገዛችለት ዝናም ለዘር፥ ጠል ለመከር የማትሰጥ ሆናለች። ፩ኛነገ ፲፯፥፩፣ ያዕ ፭፥፲፯። ሠለስቱ ደቂቅ እሳቱን ገዝተውታል። ዳን ፫፥፳፯ ለነቢዩ ለዳንኤል ደግሞ አናብስት ተገዝተውለታል። ዳን ፮፥፳፪።

፩፥፫ ካህን አድርገው ፈጥረውታል

            አዳም በገነት እያለ ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኝበት፥ አምልኮቱን የሚፈጸምበት በዓት (ቦታ) ነበረው። ሀብተ ክህነት ተሰጥቶት ስለነበር፦ መሥዋዕት ያሳርግ ነበር። ለዚህም ምስክሩ የነቢያት አለቃ ሙሴ በምድር ቤተ መቅደስ አንዲሠራ በተነገረው ጊዜ፦ ሥርዓቱን ሁሉ ልክ በሰማይ ቤተ መቅደስ እንዳየው አይነት እንዲያደርገው በማስጠንቀቂያ ጭምር መታዘዙ ነው። ዘጸ ፲፭፥፲። በሰማይ መሠዊያና መሥዋዕት ፥ ጸሎትና ምልጃም እንዳለ በራእይ ዮሐንስ ተገልጧል። «አምስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለጠበቁት ምስክር የተገደሉትን ሰዎች ነፍሳት ከመሠዊያው በታች አየሁ። በታላቅ ድምፅም እየጮኹ፦ «ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ፥ እስከመቼ ድረስ አትፈርድም? ስለ ደማችንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም? አሉ። ለእያንዳንዱም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፤» ይላል። ራእ ፮፥፱። በተጨማሪም፦ «ሌላ መልአክም መጣ፤ በመሠዊያው ፊትም ቆመ፤ የወርቅ ጥናም ይዞ ነበር፤ በዙፋኑ ፊት ባለው በወርቁ መሠዊያም ላይ፥ ለቅዱሳን ሁሉ ጸሎት እንዲያሳርገው ብዙ ዕጣን ተሰጠው። የዕጣኑም ጢስ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር ከመልአኩ እጅ ወደ እግዚአብሔር ፊት ዐረገ።» የሚልም አለ። ራእ ፰፥፫። ስለዚህ አዳምም በገነት መሥዋዕት የሚያሳርግበት የመሠዊያ ቦታ ነበረው መባሉ ትክክል ነው። ነቢዩ ኢሳይያስም፦ «ከሱራፌልም አንዱ እየበረረ ወደ እኔ መጣ፥ በእጁም ከመሠዊያው በጉጠት የወሰደው ፍም ነበረ፥ አፌንም ዳሰሰበትና፦ እነሆ፥ ይህ ከንፈሮችህን ነክቶአል፤ በደልህም ከአንተ ተወገደ፥ ኃጢአትህም ተሰረ የለህ፥ አለኝ።» ብሏል። ኢሳ ፮፥፮።

            በሌላ በኩል ደግሞ ቀዳማዊ አዳም ለዳግማዊ አዳም፥ ለኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ በመሆኑ ከዚያ አንፃር የምንረዳው ብዙ ነገር አለ። ቀዳማዊ አዳም ከድንግል መሬት እንደተገኘ፥ ዳግማዊ አዳም ኢየሱስ ክርስቶስ ከድንግል ማርያም ተወልዷል፤ እርሱም የባህርይ ንጉሥ ነው። ፩ኛ ጢሞ ፩፥፲፯። ፪ኛ ጴጥ ፩፥፲፩። እንደ መልከ ጸዴቅክህነትም የዘለዓለም ካህን ነው ዕብ ፭፥፮፤ ፱፥፲፩። እንግዲህ አዳም ለክርስቶስ ምሳሌ ሊሆን የቻለው በጸጋ ካህንም ንጉሥም በመሆኑ ነው። መቅድመ ገድለ አዳም ላይ፦ «ዐርብ ዕለትም ስድስተኛ ቀን ሆነ፤ ፀሐይ ከወጣ በኋላ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ አዳምን ፈጠሩት፤ በፊታቸውም ቆመ፥ የሕይወት እስትንፋስም እፍ አሉበት፤ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ሀብተ ክህነትን፣ ሀብተ መንግሥት፥ሀብተ ትንቢትን ሰጡት።» ይላል።

፩፥፬ ፦ ነቢይ አድርገው ፈጥረውታል፤
ከላይ እንደተገለጠው፦ አባታችን አዳም፦ ሀብተ ትንቢት ተሰጥቶት ስለነበር ፦ የራቀው ቀርቦ ፥ የረቀቀው ጐልቶ እየተገለጠ ለት ትንቢት ይናገር ነበር። በገድለ አዳም እንደተጻፈው ከመሞቱ በፊት ለልጁ ለሴት፦ «ልጄ ሆይ! በኋላኛው ዘመን ጥፋት ይመጣል ፥ ፍጥረትን ሁሉ ያሰጥማል ፥ ከስምንት ሰው በቀር የሚቀር የለም። ልጄ ሆይ ! ከልጆቻችሁ የሚቀሩት እኒህ በዚህ ዘመን ከዚህ ቤት ሥጋ ዬን ከእነርሱ ጋር (ከወርቁ ፥ ከከርቤው ፥ ከዕጣኑ ጋር) ይወስዱታል።» እያለ ነግሮታል። ይህም የኖኅን ዘመን ጥፋት የሚያመለክት ነበር።
፪፦ ሰባቱ ባህርያት ፤
            «ሰብእ» ማለት ሰባት ማለት ነው። እንዲህም የተባለበት ምክንያት ከሰባቱ ማለትም ከአራቱ ባህርያተ ሥጋና ከሦስቱ ባህርያተ ነፍስ ስለተፈጠረ ነው። የሰው ልጅ የተፈጠረባቸው አራቱ ባህርያተ ሥጋ የተገኙት፦ አፈር ከዱዳሌብ ፥ ውሃ ከናጌብ ፥ ነፋስ ከአዜብ ፥ እሳት ከኮሬብ ነው። ሦስቱ ባህርያተ ነፍስ ደግሞ ለባዊነት (ማሰብ) ፥ ነባቢነት (መናገር) ፥ ሕያውነት (ዘለዓለማዊነት) ናቸው። ሰባት ፍጹም ቁጥር እንደሆነ ሁሉ ከሰባቱ ባሕርያት የተፈጠረ የሰው  ልጅም ፍጹም ሆኖ ተፈጥሯል።

፫ ፦ በአራቱ ባሕርያተ ሥጋ እግዚአብሔርን መምሰል፤
            እግዚአብሔር አዳምን ከአራቱ ባህርያተ ሥጋ የፈጠረው ፦ በአምላካዊ ባህርዩ ውስጥ አራት ነገሮች እንዳሉ ለማጠየቅ ነው። እነኚህም፦ ባለጠግነት ፥ ሩኅሩኅነት (ቸርነት) ፥ ከሃሊነት (ሁሉን ቻይነት) ፥ እና ፈታሒነት (ፈራጅነት ፥ ዳኝነት) ናቸው። በዚህም መሠረት ፦ መሬት የባለጠግነቱ ፥ ውኃ የርኅራኄውና የቸርነቱ ፥ እሳት የከሃሊነቱ ፥ ነፋስ ደግሞ የፈታሒነቱ ምሳሌ ናቸው።
፫፥፩ መሬት፤
             ባዕለጸጋ የሆነ እግዚአብሔር የመሬትን ብልጽግና አብዝቷል። ቅዱስ ዳዊት፦ «ምድርን ጐበኘሃት ፥ ብልጽግናዋንም እጅግ አበዛህ ፤»  ያለው ለዚህ ነው። መዝ ፷፬፥፱። በተጨማሪም  ፦ « እግዚአብሔር ይሁብ ምሕረቶ ፥ ወምድርኒ ትሁብ ፍሬሃ ፤ እግዚአብሔር በጎ ነገርን ይሰጣል ፥ ምድርም ፍሬዋን ትሰጣለች፤» በማለት ተናግሯል። መዝ ፹፬፥፲፪። ይህም የሁሉ ነገር አስገኝ እግዚአብሔር እንደሆነ ሁሉ ፥ ከመሬ ትም ያልተገኘ ፥ የማይገኝም ነገር የለም ፥ ለማለት ነው። በመሆኑም የሰው ልጅ በመሬትነት ባህርዩ ፥ በባህርዩ ባዕለጸጋ የሆነውን እግ ዚአብሔርን ይመስለዋል።
፫፥፪ ፦ ውኃ፤
            ውኃ፦ ለእግዚአብሔር ርኅርኄና ቸርነት ምሳሌ ነው። የውኃ ባህርይ እድፍ ማስወገድ ፥ ቆሻሻ ማጥራት ነው። እግዚአብ ሔርም አይሠሩ ሥራ ሠርተው ፥ በድለው ፦ « አላበጀንም ፥ ማረን ፥ ይቅር በለን፤» ካሉት፦ ሁሉን ይቀበላል ፥ ሁሉን ይምራል፤ ከኃጢአ ታቸው ያነጻቸዋል ፥ ከበደላቸው ያጥባቸዋል። ይኽንንም የሚያደርገው በውኃ በተመሰለ ርኅራኄውና ቸርነቱ ነው። ቅዱስ ዳዊት ይኽ ንን አውቆ፦ «አቤቱ ፥ እንደ ቸርነትህ መጠን ማረኝ ፤ እንደ ምሕረትህም ብዛት መተላለፌን ደምስስ። ከበደሌ ፈጽሞ እጠበኝ ፥ ከኃጢ አቴም አንጻኝ ፤» ብሏል። መዝ ፶፥፩። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም «ወይስ ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደማይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ ፤ ሴሰኞች ቢሆኑ ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች (ወንድ ከወንድ፥ ሴት ከሴት የሚያመነዝሩ) ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። ከእናንተም አንዳንዶች እንደዚህ ነበራችሁ፤ ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል ፥ ተቀድሳችኋል ፥ ጸድቃችኋል፤» ብሏል። ፩ኛ ቆሮ ፮፥፱። በመሆኑም የውኃነት ባሕርይ ያለው የሰው ልጅ በርኅራኄውና በቸርነቱ በንስሐ ውኃ ከኃጢአት የሚያነጻውንና ከበደል የሚያጥበውን እግዚአብሔርን ይመስላል።
፫፥፫፦ እሳት፤
            እሳት፦ ለእግዚአብሔር ከሃሊነት(ሁሉን ቻይነት) ምሳሌ ነው። እሳት በተነሣ ጊዜ እርጥቡንም ደረቁንም ያቃጥላል፥ እንዲያ ውም ገደልና ባሕር ካልከለከለው በስተቀር የብዙ ቀን መንገድ እየተጓዘ ማንኛውንም ነገር አቃጥሎ ወደ አመድነት መለወጥ ይችላል። እግዚአብሔርም ቸርነቱና ርኅራኄው ካልከለከለው በስተቀር ሁሉን ላጥፋ ቢል ይቻለዋል፥ የሚሳነው ነገር የለም ዘፍ ፲፰፥፲፬ ፣ ሉቃ ፩፥፴፯።
            እግዚአብሔር ለሙሴ በደብረ ሲና በእሳት አምሳል ሐመልማሏን ተዋሕዶ ተገልጦለታል። ዘዳ ፫፥፪። እሳቱ ያላቃጠላት ሐመልማል የእመቤታችን የቅድሳት ድንግል ማርያም ምሳሌ ናት። ምክንያቱም እመቤታችንም በተለየ አካሉ በማኅፀኗ ያደረው እሳተ መ ለኰት አላቃጠላትምና ነው። ሊቀ ነቢያት ሙሴ ፦ «እግዚአብሔር አምላክህ የሚበላ (የሚያቃጥል) እሳት ፥ ቀናተኛም አምላክ ነውና።» በማለት ወገኖቹን እስራኤልን አሰጠንቅቋቸዋል። ዘዳ ፬፥፳፬። ነቢዩ ኢሳይያስም፦ « እነሆ ፥ እግዚአብሔር፦ መዓቱን በቊጣ ፥ ዘለፋ ውንም በእሳት ነበልባል ይመልስ ዘንድ ከእሳት ጋር ይመጣል፤ » ብሏል። ኢሳ ፷፮፥፲፭። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ፦ «አምላካችን በእውነት የሚያጠፋ እሳት ነውና፤» በማለት ተመሳሳይ ነገር ተናግሯል። ዕብ ፲፪፥፳፱። በመሆኑም የእሳትነት ባህርይ ያለው የሰው ልጅ ፈጣሪውን እግዚአብሔርን ይመስለዋል።
፫፥፬፦ ነፋስ፤
            ነፋስ ፦ ለእግዚአብሔር ፈታሒነት(ፈራጅነት ፥ዳኝነት) ምሳሌ ነው። ገበሬ አዝመራውን አጭዶ ፥ ከአውድማ ላይ ወቅቶ ፥ በመንሽ ባነሣው ጊዜ ፥ በነፋስ ኃይል፦ ፍሬው ከገለባ ፥ ገለባውም ከፍሬው ይለያል። ጌታም በፈታሒነቱ ጻድቃንን ከኃጥአን ፥ ኃጥአ ንንም ከጻድቃን ይለያል። መጥምቀ መለኰት ቅዱስ ዮሐንስ፦ «መንሹም በእጁ ነው ፥ አውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል፥ ስንዴውንም በጎተራ ይከታል፥ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል፤» ያለው ለዚህ ነው። ማቴ ፫፥፲፪ ፣ ሉቃ ፫፥፲፯። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ስለ ፍርድ ቀን በተናገረ ጊዜ ፦ «እረኛም፦ በጎቹን ከፍየሎቹ እንደሚለይ እርስ በእርሳቸው ይለያ ቸዋል፤ በጎቹን በቀኙ ፥ ፍየሎቹን በግራው ያቆማቸዋል።» ብሏል። ማቴ ፳፭፥፴፪። ጻድቃን በስንዴና በበጎች ሲመሰሉ ኃጥአን ግን  በገለባና በፍየሎች ተመስለዋል። እንግዲህ የሰው ልጅ በነፋስነት ባህርዩ ፈጣሪውን እግዚአብሔርን እንደሚመስለው በዚህ እናስ ተውላለን።
በሦስቱ ባሕርያተ ነፍስ እግዚአብሔርን መምሰል፤
            ነፍስ፦ ለባዊት ናት ፥ ልብ ታደርጋለች ፥ ታስባለች ፤ ነባቢትም ናት ፥ ቃል አላት ፥ ትናገራለች ፤ ሕያዊትም ናት ፥ ለዘለዓለም ትኖራለች። ለባዊነት የሚለው ቃል በቁም ሲተረጐም፦ ልባም ፥ ልብ አድራጊ ፥ ተመልካች ፥ አስተዋይ ፥ ብልኅ ፥ ዐዋቂ ፥ ጠንቃቂ ማለት ነው። በመጽሐፈ ሲራክ ፦ «ነገርን ዐዋቂዎች ራሳቸው በልቡናቸው ይራቀቃሉ ፥ የተረዳ ምሳሌም ይናገራሉ፤ » የሚል ተጽፏል። ሲራ ፲፰፥፳፰። በመጽሐፈ ጥበብ ደግሞ ፦ «ሰው ወዳጅ ፥ የጥበብ ወዳጅዋ ፥ ዐዋቂ ፥ እውነተኛ ፥ ግዳጅ የሌለበት ፥ ትዕግሥተኛ ፥ ሁሉንም የሚችል ፥ ሁሉንም የሚጐበኝ ፥ ንጹሓትና አስተዋዮች ፥ ረቂቃትም በሆኑ ነፍሳት የሚያድር ነው፤» የሚል አለ። ጥበብ ፯፥፳፫።
            ነፍስ ከሥጋ ከተለየች በኋላ አስባ እንደምትናገር (ነባቢት እንደሆነች) ሕያውም ሆና እንደምትኖር፦ ቅዱስ ዮሐንስ በራእይ ያየውን ፦ «ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ጠበቁት ምስክር የተገደሉትን ሰዎች ነፍሳት ከመሠዊያው በታች አየሁ። በታላቅ ድምፅ እየ ጮኹ፤» በማለት ተናግሯል። ራእ ፮፥፱። ይኽንንም ጌታም በወንጌል ፦ « ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ ፥ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል ፤ ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም፤» በማለት አስቀድሞ ለእኅተ አልዓዛር ማርታ ነግሯት ነበር። ዮሐ ፲፩፥፳፭።
            እንግዲህ ለባዊነት የሚለው ልብን ፥ ነባቢት የሚለው ቃልን ፥ ሕያዊት የሚለው ደግሞ ሕይወትን እንደሆነ አይተናል። በም ሥጢረ ሥላሴ፦ አብ ልብ ፥ ወልድ ቃል ፥ መንፈስ ቅዱስ ሕይወት እስትንፋስ ናቸው። አብ የራሱንም ሆኖ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ልባቸው ነው ፤ ወልድ የራሱንም ሆኖ የአብ የመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው ነው ፤ መንፈስ ቅዱስም የራሱንም ሆኖ የአብ የወልድ ሕይወ ታቸው እስትንፋሳቸው ነው። ልብን በተመለከተ ነቢዩ ኢሳይያስ ፦ «የእግዚአብሔርን ልብ ያወቀው ማነው? » በማለት ተናግሯል። ኢሳ ፵፥፲፫ ፣ ሮሜ ፲፮፥፴፬ ። ቅዱስ ዳዊት ደግሞ ሦስቱንም ልብ ፥ ቃልና እስትንፋስን በተመለከተ «የእግዚአብሔር ይቅርታው (የአብ ቸር ነቱ) ምድርን ሞላ። በእግዚአብሔር ቃል (በወልድ) ሰማዮች ጸኑ ፥ (ባለማለፍ ጸንተው የሚኖሩት ሰባቱ ሰማያት ተፈጠሩ) ፥ ሠራዊ ታቸውም ሁሉ በአፉ እስትንፋስ ፤ (በመንፈስ ቅዱስ) ፤» በማለት ተናግሯል። መዝ ፴፪፥፭። በመሆኑም፦ ነፍስ በለባዊነት አብን ፥ በነባቢነት ወልድን ፥ በሕያውነት መንፈስ ቅዱስን ትመስላለች።
እግዚአብሔርን መምሰል፤ (በጸጋ በመክበር)

3 comments:

 1. KALEHIWOTYASEMALIN , MENGISTE SEMAYATIN YAWERESILIN, YAGELIGLWOT ZEMENON YABZALIN.
  BERTULIN ABATACHIN.

  ReplyDelete
 2. kale hiwot yasemalen, mengeste semayaten yawreselen, edme tena yestelen.

  ReplyDelete
  Replies
  1. kale hiwot yasemalen, mengeste semayaten yawreselen, edme tena yestelen.


   Delete