Saturday, November 20, 2010

ነገረ ቅዱሳን ክፍል ፬

፮፦ ቅዱሳት ንዋያት፤

በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በውስጥ በአፍአ የምንገለገልባቸው ንዋያት (እቃዎች) የተቀደሱ ናቸው። ለዓለ ማዊ ወይም ለሥጋዊ አገልግሎት አንጠቀምባቸውም። ለእግ ዚአብሔር የተለዩ ናቸው። «በቀማሚም ብልሃት እንደተሠራ ቅመም የተቀደሰ የቅብዐት ዘይት ታደርገዋለህ፤ የተቀደሰ የቅብዐት ዘይት ይሆናል። የምስክሩንም ድንኳን፥ የምስ ክሩንም ታቦት፥ ገበታውንም ዕቃውንም ሁሉ፥ መቅረዙንም፥ ዕቃውንም፥ የዕጣን መሠዊያውንም፥ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን መሠዊያና ዕቃውንም ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሰንና መቀመጫውንም ትቀባበታለህ። ሁሉንም ትቀድሳቸዋለህ፤ ቅድስተ ቅዱሳንም ይሆናሉ፥ የሚነካቸውም ሁሉ ቅዱስ ይሆናል፤» ይላል። ዘጸ ፴፥፳፭-፳፱። በአዲስ ኪ ዳንም አዲስ ቤተ መቅደስ ተሠርቶ የሚከብረው ፥ ቅዱሳት ንዋያትም የሚከብሩት ፥ ቅብዐ ሜሮን እየተቀቡ ነው። በመሆኑም፦ ታቦቱ ፥ መንበሩ ፥ ጻሕሉ ፥ ዐውዱ ፥ አጎበሩ ፥ እርፈ መስቀሉ ፥ ጽዋው ፥ መቊረርቱ ፥ ብርቱ ፥ ከበሮው ፥ ጸናጽሉ ፥ መቋሚያው ፥ ጃንጥላው ፥ ድባቡ ፥ ምንጣፉ ፥ መጋረጃው ፥ መነሳነሱ ፥ መቅረዙ ፥ አትሮንሱ ፥ ሙዳዩ ፥ መሰቦ ወርቁ ሁሉም የተቀደሱ ናቸው።

፯፦ ቅዱሳት አልባሳት፤

በእግዚአብሔር ቤት ካህናት ለብሰውት የሚያገለግሉበት አልባሳት ሁሉ የተቀደሱ ናቸው። በሥጋዊ ልብስ እግዚአብሔር አይገለገልም። ለእግዚአብሔር የተለዩ መንፈሳውያት አልባሳት አሉ። «አንተም ወንድምህን አሮንን  ከእርሱም ጋር ልጆቹን ከእስራኤል ልጆች መካከል ለይተህ በክህነት ያገለግሉኝ ዘንድ ወደ አንተ አቅርብ፤ አሮንን ፥ የአሮንንም ልጆች፥ ናዳብን፥ አብድዩንም፥ አልዓዛርንም፥ ኢታምርንም፥ አቅርብ። የተቀደሰውንም ልብስ ለክብርና ለመለያ እንዲሆን ለወንድምህ ለአሮን ሥራለት። አንተም የጥበብ መንፈስ ለሞላሁባቸው በልባቸው ጥበበኞች ለሆኑት ሁሉ ተናገር። እነርሱም ካህን ሆኖ እንዲያገለግለኝ ለአሮን ለቤተ መቅደስ የሚሆን የተለየ ልብስ ይሥሩ። የሚሠሯቸውም ልብሶች እነዚህ ናቸው፤ ልብሰ እንግድዐ፥ ልብሰ መትከፍ፥ ቀሚስም፥ ዥንጉርጉር እጀ ጠባብ፥ መጠምጠሚያ፥ መታጠቂያም፤ እነዚህንም በክህነት ያገለግሉኝ ዘንድ ለወንድምህ ለአሮን፥ ለልጆቹም የተቀደሰ ልብስ ያድርጉ። ሰማያዊና ሐምራዊ፥ ቀይ ግምጃ፥ ጥሩ በፍታም ይውሰዱ።» ይላል። እግዚአብሔር ለሙሴ የነ ገረው አሠራሩን ጭምር ነው። ዘጸ ፳፰፥፩-፲፬። በነቢዩ በሕዝቅኤልም አድሮ፦ «ወደ ውጭውም አደባባይ በወጡ ጊዜ ያገለገሉበትን ልብሳቸውን (ልብሰ ተክህኖውን) ያውልቁ፤ በተቀደሰውም ዕቃ ቤት ያኑሩት፤ ሕዝቡን በልብሳቸው እንዳይቀደሱት ሌላውን ልብስ ይልበሱ።» ብሏል። ይህም ልብስ ተክህኖ ለብሶ ዓለማዊ ቦታ መገኘት እንደማይገባ ያስረዳል። ሕዝ ፵፬፥፲፱። በመ ሆኑም፦ ቀሚሱ ፥ ካባ ላንቃው ፥ መጎናጸፊያው ፥ ቀጸላው ፥ ሞጣህቱ ፥ አክሊላቱ ፥ ቆቡ ፥ ማኅፈዳቱ ሁሉም የተቀደሱ ናቸው።

፰፦ጻድቅ

          ጻድቅ፦ እውነተኛ ማለት ነው። በመሆኑም ጻድቅ እግዚአብሔር ነው። «በእውነትህ ቀድሳቸው፥ ቃልህ እውነት ነው፤» እንዲል ፥ እውነት የባህርይ ገንዘቡ ነው። ዮሐ ፲፯ ፥፲፯። እርሱ የእውነትና የሕይወት መንገድ ነው። ዮሐ ፲፬፥፮። ጸጋንና እውነትን የተመላ ነው። ዮሐ ፩፥፲፩። «ኦሪት በሙሴ ተሰጥታን ነበርና፥ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነልን፤ » የተባለው ለዚህ ነ ው። ዮሐ ፩ ፥፲፯ ይኸንን በተመለከተ በመጽሐፈ ዕዝራ፦ « አቤቱ የእስራኤል አምላክ ሆይ ፥ አንተ ጻድቅ ነህ፤ » የሚል አለ። ዕዝ ፱፥፲፭። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ግዳጁን አንደጨረሰ፥ የሚያርፍበት ዕድሜ እንደደረሰ፥ መልካሙን ገድል እንደተጋደለ፥ ሩጫውን እንደፈጸመ፥ ሃይማኖቱንም እንደጠበቀ ከተናገረ በኋላ፦ «እንግዲህስ የጽድቅ አክሊል ይቆየኛል፤ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው እግዚአብሔር በዚያ ቀን ለእኔ ያስረክባል፤ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱ ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም።» ብሏል። ፪ኛ ጢሞ ፬፥፮-፰

፰፥፩፦ ጻድቃን፤

          አካኼዳቸውን በእግዚአብሔር ፊት ያደረጉ፥ ሃይማኖት ይዘው ፥ ምግባር ሠርተው የተገኙ ሰዎች ጻድቃን ይባላሉ። እነኚህም በነገር ሁሉ እውነተኞች ሆነው የተገኙ ናቸው። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ስለ ኃጥአን እና ስለ ጻድቃን በተናገረበት አንቀጽ፦ «ኃጢአትን የሚሠራት ሁሉ እርሱ በደልን ደግሞ ያደርጋል፥ ኃጢአት በደል ናትና። (ጥቃቅኑን ኃጢአት የሚሠራ ወደ ታላላቁም ኃጢአት ተስቦ ይበድላል፥ ሁለቱም ከመንግሥተ ሰማያት በማውጣት አንድ ናቸው)። እርሱም ኃጢአትን ያስወግድ ዘንድ እንደተገለጠ ታውቃላችሁ፥ በእርሱም ኃጢአት የለም። በእርሱ የሚኖር ሁሉ አይበድልም፥ (አንድ ጊዜ ቢበድል ሁለተኛ፥ በሥጋ ቢበድል በነፍስ፥ በሐልዮ ቢበድል ፥ በነቢብ በገቢር አይበድልም)፥ የሚበድልም ሰው አያየውም፥ አያውቀውምና። (አያምነውምና፥ አይወደውምና)። ልጆቼ ሆይ ማንም አያስታችሁ፤ (ጥቃቅኑ ኃጢአት ወደ ታላላቁ ኃጢአት አያደርሷችሁም፥ ጥቃቅኑና ታላላቁ ከመንግሥተ ሰማያት በማውጣት አንድ አይደሉም፥ በማለት ማንም አያታላችሁ)፤ እርሱ ጻድቅ እንደሆነ ጽድቅን የሚያደርግ ሁሉ ጻድቅ ነው።» ብሏል። ፩ኛ ዮሐ ፫፥፬-፯።

          በብሉይ ኪዳን፦ «የኖኅ ትውልድ እንዲህ ነው፤ ኖኅም በትውልዱ ጻድቅ፥ ፍጹምም ሰው ነበረ፤ ኖኅም እግዚአብሔርን ደስ አሰኘው፤» ተብሎ ለኖኅ ተጽፎለታል። ዘፍ ፮፥፱። እግዚአብሔርም፦ «በዚህ ትውልድ በፊቴ ጻድቅ ሆነህ አይቼሃለሁና።» ሲል መስክሮለታል። ዘፍ ፯፥፩። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከዚህ ተነሥቶ፦ «ኖኅም ሰለማይታየው ነገር የነገሩትን ባመነ ጊዜ ፈራ፥ ቤተሰቡንም ያድን ዘንድ ክፍል ያላትን መርከብ ሠራ፥ በዚህም ዓለምን አስፈረደበት፥ በእምነትም የሚገኘውን ጽድቅ ወራሽ ሆነ።» በማለት ተናግሮለታል። ዕብ ፲፩፥፯።

          ቅዱስ ዳዊት ጻድቃንን በተመለከተ ብዙ ተናግሯል። በተለይም የጸጋቸውንና የክብራቸውን ብዛት ሲናገር፦ «ጻድቅሰ ከመ በቀልት ይፈሪ። ጻድቅ እንደ ዘንባባ ያፈራል።»ብሏል። መዝ ፺፩፥፲፪ ዘንባባ አድጐ ከምድር ወደ ሰማይ ከፍ እንደሚል ፥ የጻድቅም ጸጋው ክብሩ ከፍ ያለ ነው፥ ሰማያዊ ነው። የዘንባባ ፍሬው ብዙ እንደሆነ የጻድቅም ጸጋው ክብሩ ብዙ ነው፤ ብሏል። በሌላ በኩል ደግሞ ዘንባባ የደስታ ምልክት ነው። አብርሃም ይስሐቅን፥ ይስሐቅ ደግሞ ያዕቆብን በወለዱ ጊዜ፤ እስራኤል ዘሥጋ ከባርነት ቤት ከግብፅ በወጡ ጊዜ ዘንባባ ይዘው አመስግነዋል። ጻድቃንም የደስታ ምልክት ማለትም ሰውንም እግዚአብሔርንም ደስ ያሰኙ ናቸው። ዘንባባ የድል ምልክት ነው። ዮዲት የእስራኤልን ጠላት ሆሎፎርኒስን በገደለችው ጊዜ የእስራኤል ሴቶች ተሰብስበው መርቀዋታል፥ በዓልም አድርገውላታል። እርሷም ለእያንዳንዳቸው ዘንባባ አድላቸዋለች። ዮዲ ፲፭፥፲፪። ጻድቃንም ፍትወታት እኲያትን፥ ርኲሳት መናፍስትን ድል ያደረጉ ናቸው። ዘንባባ የሰላም ምልክት ነው። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜ ዘንባባ ይዘው ተቀብለውታል። ዮሐ ፲፪፥፲፫። ቅዱስ ጳውሎስ፦ «ቢቻላችሁ በእናንተ በኲል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ።» እንዳለ ሮሜ ፲፪፥፲፰ ጻድቃንም ለጠላቶቻቸውም ጭምር የሰላም ሰዎች ነበሩ። ሰላምን ሲሹ ሰላምን ሲከተሉ የኖሩ ናቸው። መዝ ፴፫፥፲፬።

          ቅዱስ ዳዊት መንግሥተ ሰማያት የጻድቃን መሆኗንም ተናግሯል። ምክንያቱም የጸጋና የክብር መጨረሻ መንግሥተ ሰማያት ናትና። «አርኀዉ ሊተ አናቅጸ ጽድቅ፥ እባእ ውስቴቶን ወእግነይ ለእግዚአብሔር። ዛ አንቀጽ እንተ እግዚአብሔር፥ ጻድቃን ይበውኡ ውስቴታ። የጽድቅን ደጆች ክፈቱልኝ፥ ወደ እነርሱ ገብቼ እግዚአብሔርን አመሰግን ዘንድ። ይህች የእግዚአብሔር ደጅ ናት፥ ወደ እርስዋ ጻድቃን ይገባሉ።» ብሏል። መዝ ፻፲፯፥፲፱። ይህም ከዚያ ገብቼ ለእግዚአብሔር እገዛ ፥ እር ሱንም አገለግል ዘንድ ፥ የኢየሩሳሌምን አንድም የቤተ መቅደስን አንድም የገነትን ደጆች ክፈቱልኝ። ይህች የኢየሩሳሌም አንድም የቤተ መቅደስ አንድም የገነት ደጆች የእግዚአብሔር ናት። (የእግዚአብሔር በረከትና ሕይወት የታዘዘባት ናት)። ጻድቃን ይወርሷታል፥ ማለት ነው። በሌላ አንቀጽም፦ «ጻድቃንሰ ይወርስዋ ለምድር፥ ወይነብሩ ውስቴታ ለዓለም ዓለም። ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፥ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ። » ብሏል። ምድር ያለውም፦ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር የተባለችውን፥ ቅዱስ ዮሐንስ በራእይ ያያትን መንግሥተ ሰማያትን ነው። ራእ ፳፩፥፩።

          ወልደ ዳዊት ንጉሥ ሰሎሞንም በአንድ ምዕራፍ ላይ ብቻ ስለ ጻድቃን ብዙ ተናግሯል።
-       ስለ በረከት፦ «በረከተ እግዚአብሔር ውስተ ርእሰ ጻድቃን። የእግዚአብሔር በረከት በጻድቃን ራስ ላይ ነው።»

-       በመታሰቢያቸው እለት ልዩ ምስጋና ማቅረብ እንደሚገባ፦ «ዝክረ ጻድቅ ምስለ ውዳሴ። የጻድቅ መታሰ ቢያ ከምስጋና ጋር ነው።»

-       ስለ አንደበታቸው « ነቅዓ ሕይወት ውስተ አፈ ጻድቃን፤ የሕይወት ምንጭ በጻድቃን አፍ ነው፤ (የሕይወት መገኛ የሚሆኑ ሕግጋተ እግዚአብሔር በእነርሱ አፍ ሲነገር ይኖራል።)

-       ስለ ደመወዛቸው፦ «ግብረ ጻድቃን ሕይወቱ ይገብር፤ የጻድቃን ሥራ ሕይወትን ያደርጋል፤ (የድካማቸው ዋጋ ሕይወት ነው፤)»

-       ስለነገራቸው ጽሩይነት፦ «ብሩር ርሱን ልሳነ ጻድቅ፤ የጻድቅ ምላስ (ነገራቸው) የተፈተነ (የነጠረ) ብር ነው፤»

-       ሀብተ ትንቢት እንደተሰጠቸው፦ «ከናፍረ ጻድቃን የአምራ ነዋኃ፤ የጻድቃን ከንፈሮች የሩቁን ያውቃሉ፤ (መጻእያትን ይናገራሉ)፤»

-       በረከታቸው ሁሉን ዕለጸጋ እንደምታደርግ፦ «በረከተ እግዚአብሔር ውሰተ ርእሰ ጻድቃን ፥ ይእቲ ታብእል፤ የእግዚአብሔር በረከት በጻድቃን ራስ ላይ ሆና ባለጠጋ ታደርጋለች፤»

-       ስለ ምኞታቸው፦ «ፍትወቱ ለጻድቅ ሥምርት በኀበ እግዚአብሔር። የጻድቅ ምኞቱ ግን በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደች ናት፤»

-       ከኃጢአት ፈጽመው ተለይተው እንደሚኖሩ፦ «ጻድቅሰ ተግሂሦ ለዓለም ይድኀን፤ ጻድቅ ግን ተሰውሮ ለዘለዓለም ይድናል፤»
               
-       ደስታ እንደማይለያቸው፦ «ትጐነዲ ተፍሥሕት ምስለ ጻድቃን፤ ተድላ ደስታ ከጻድቃን ጋር ትኖራለች፤»

-       በምንም እንደማይናወጡ፦ «ጻድቅሰ ለዓለም ኢይኤብስ፤ ጻድቅ ሰው ለዘላለም አይናወጥም፤ (አይበድልም)፤»

-       ጥበብ መንፈሳዊ ከአንደበታቸው እንደማይለይ፦ «አፈ ጻድቃን ይነብብ ጥበበ፤ የጻድቃን አፍ ጥበብን ይናገራል፤»

-       ስለ ዕውቀታቸው፦ «ወከናፍረ ጻድቃን ያውኀዝ ሞገሰ፤ የጻድቃን ከንፈሮች ሞገስን ያፈስሳሉ፤ (የተወደደ ዕውቀትን ይናገራሉ)፤» በማለት ተናግሯል። ምሳ ፲፥፩-፴፪።

በአዲስ ኪዳን ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ስለ ካህኑ ዘካርያስና ስለ ሚስቱ ኤልሳቤጥ ጽድቅ በወንጌሉ መጀመሪያ መስክሯል። «በይሁዳ ንጉሥ በሄሮድስ ዘመን ከአቢያ ክፍል የሆነ ዘካርያስ የሚባል አንድ ካህን ነበረ። ሚስቱም ከአሮን ልጆች ወገን ነበረች፥ ስምዋም ኤልሳቤጥ ነበረ። ሁለቱም በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ። በእግዚአብሔር ሥርዓትና በትእዛዙ ሁሉ ያለ ነውር የሚሄዱ ነበሩ ልጆችም አልነበራቸውም፥ ኤልሳቤጥ መካን ነበረችና፥ ዘመናቸውም አልፎ ነበር።» ብሏል። ሉቃ ፩፥፭-፯። የሊቀ ካህናቱ የአሮን ሚስት ስሟ ኤልሳቤጥ ትባል ነበር። እርሷ ሳለች ኦሪት ተሠርታለች። በኋለኛዋ ኤልሳቤጥ ግን አልፋ ወንጌል ተሠርታለች። በኤልሳቤጥ የተሠራች ሕግ በኤልሳቤጥ አለፈች ለማለት ኤልሳቤጥን ጠቅሷል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ፦ «የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው ፤» ብሏል። ሮሜ ፰ ፥ ፴። ከሁሉም በላይ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፦ «ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል።» በማለት ስለ ጻድቃን ተኗግሯል። ማቴ ፲፥፵፩።

3 comments:

  1. ቀሲስ እግዚአብሔር አምላክ ቃለ ሕይወትን ያሰማልን፤ የአገልግሎት ዘመንዎን ይባርክልን፤ የቅዱሳን አምላክ ይጠብቅልን፡፡ አስበ መምህራንን ይስጥልን፡፡

    ReplyDelete
  2. Kesis kale hiwot yasemalin behiwot betena yitebekelin!

    ReplyDelete
  3. Kesis kale hiwot yasemalin behiwot betena yitebekelin!

    ReplyDelete