Sunday, November 14, 2010

« ዛሬ የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፤ ማቴ ፩÷፬ »

        ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራው ስብከቱ ፥ በአንቀጸ ብጹዓን ትምህርቱ፡- «ብፁዓን እለ ይላህዉ ይእዜ እስመ እሙንቱ ይትፌሥሑ፤ « ዛሬ የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው ፥ እነርሱ ደስ ይሰኛሉና፤ (መጽናናትን ያገኛሉና)፤» ብሏል።  ቅዱሳን ሐዋርያትም በዚህ ላይ ተመስርተው፦ « እናንተ ኃጥአን እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት ዐሳብም ያላችሁ እናንተ ልባችሁን አጥሩ። እዘኑና አልቅሱ፤ ሳቃችሁን ወደ ልቅሶ፥ ደስታችሁንም ወደ ኀዘን መልሱ ፥ በእግዚአብሔር ፊት ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤ እርሱም ከፍ ከፍ ያደርጋችኋል። » እያሉ አስተምረዋል። ያዕ ፬፥፱ ኀዘን ሲባል ሁለት ዓይነት ነው። አንደኛው የማይገባ ኀዘን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የሚገባ ኀዘን ነው።

፩፡- የማይገባ ኀዘን፤
          እናት አባት፥ ወንድም እኅት፥ ባል ሚስት ልጅ ሞቱብኝ፥ የዚህን ዓለም ሀብት ንብረት አጣሁ ብሎ በቀቢጸ ተስፋ ማዘን የማይገባ ኀዘን ነው። ምክንያቱም እንደ እናት አባት ሥላሴ አሉና ነው። እግዚአብሔር «አንተ አቡነ፥ ወአንተ እምነ፤» ይባላል። ይኸውም ይታወቅ ዘንድ ጌታችን በወንጌል፡- «እናንተስ በምትጸልዩበት ጊዜ፡- አባታችን ሆይ፥ በሰማያት የምትኖር፥ ስምህ ይቀደስ በሉ፤» ብሎናል። ማቴ ፮፥፱። «እነኋት እናትህ።» እንዲል እመቤታችንም እናታችን ናት። ዮሐ ፲፱፥፷፯። ቅዱስ ዳዊትም፡- «እምነ ጽዮን ይብል ሰብእ፤ ሰው ሁሉ እናታችን ጽዮን አባታችን እግዚአብሔር ይላል፤» ብሏል። መዝ ፹፮፥፭። ቤተክርስቲያንም፡- ከማኅፀነ ዮርዳኖስና ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ በውስጧ ስለተወለድን (በጥምቀት የጸጋ ልጅነትን ስላገኘንባት) እናታችን ናት ዮሐ ፫፧፭፧፧ በሥርዓተ ቅዳሴ ላይ፡- «እምነ በሀ ቅድስት ቤተክርስቲያን፤ እናታችን ቅድስት ቤተክርስቲያን ሆይ ፥ ሰላም እንልሻለን፤» የምንለው ለዚህ ነው።
እንደ ወንድም እንደ እኅትም ቅዱሳን መላእክት አሉ። ጌታችን በወንጌል፡- «ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን ስንኳ እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፤ (ወንድም፥ እኅት፥ ሀብት ንብረት፥ ወገን የለውም ብላችሁ እንዳትንቁ ተጠበቁ)፤ መላእክቶቻቸው በሰማያት ሁልጊዜ በሰማያት ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉ እላችኋለሁ።» ያለው ለዚህ ነው። ማቴ ፲፭፥፲፩  ማንም ሰው የወንድም የእኅቱን ጥቃት እንደማይፈልግ ሁሉ መላእክትም እንደ ወንድም እንደ እኅት የሰውን ጥቃት አይፈልጉም። ሠለስቱ ደቂቅ፦ በስደት፥ በሞት ወንድም እኅታቸውን ቢያጡም በጥቃታቸው ጊዜ የደረሰላቸው አራተኛ ሆኖ አብሮአቸው ከእሳት የገባላቸው ፥ የታደጋቸውም ፥ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ነው። ዳን ፫፥፳፭። ዳንኤልም ወደ አናብስት ጉድጓድ በተጣለ ጊዜ አብሮት የወረደው ቅዱስ ሚካኤል ነው። ዳን ፮፥፳፪
         
          እንደ ርስት ጉልትም የማታልፍ ርስት መንግሥተ ሰማያት አለች። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- «በምድር ያለው ማደሪያ ቤታችን ቢፈርስም ፥ በሰማይ በእግዚአብሔር ዘንድ የሰው እጅ ያልሠራው ዘለዓለማዊ ቤት እንዳለን እናውቃለን። ስለ እርሱ የምንደክምለትን በሰማይ ያለውን ቤታችንን እንለብስ ዘንድ እርሱን ተስፋ እናደርጋለን።» ያለው ለዚህ ነው። ፪ኛ ቆሮ ፭፧፩ በፊልጵስዮስ መልእክቱም «አገራችን በሰማይ ነው፤» ብሏል። ፊል ፫፥፳። ቅዱስ ጴጥሮስም ደጅ የምንጠናው ሰማያዊ ርስታችንን አዲሷን ሰማይና አዲሷን ምድር ነው። ብሏል። ፪ኛ ጴጥ ፫፥፫። ከሁሉም በላይ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡- «ልባችሁ አይደንግጥ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፤ በአባቴ ቤት ብዙ ማደሪያና ማረፊያ አለ፤» በማለት የሚጨበጥ የሚታመን ተስፋ ሰጥቶናል። ዮሐ ፲፬፥፩። በዚህ ያመኑ ቅዱሳን ሥጋዊው ነገር ሁሉ ሳያሳዝናቸው ሁለን ትተው ተከትለውታል። ማቴ ፲፱፥፳፯
፩፥፩ ሰው ሲሞትብን እንዴት እንዘን?
          ሞትና መቃብር የመጨረሻ አይደሉም። ከሞት አጠገብ ሕይወት፥ ከመቃብር አጠገብ ትንሣኤ አለን። እኅተ አልዓዛር ማርታ፡- «ወንድሜ፥ በመጨረሻው ቀን እንደሚነሣ አውቃለሁ፤» ብላለች። ጌታም ትንሣኤና ሕይወት እርሱ እንደሆነ ነግሯታል። ዮሐ ፲፩፥፳፬ ። ከዚህም አስቀድሞ፡- «በመቃብር ያሉት ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ፥ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ፤» ብሎ ነበር። ዮሐ ፭፥፷፱ በሌላ በኩል ደግሞ አልዓዛርን እንደሚያስነሣው እያወቀ የፍቅሩን ያህል አልቅሶለታል። «ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ። ስለዚህ አይሁድ እንዴት ይወደው እነደነበረ እዩ አሉ፤» ይላል። ዮሐ ፲፩፥፴፭። በመሆኑም ሰው ሲሞትብን በቀቢጸ ተስፋ ሳይሆን የፍቅራችንን ያህል ልናለቅስ ይገባል። ይኸውም፡-
፩፥፪ ነፍስ ከሥጋ ስትለይ፤
          የነፍስ ሞቷ ከእግዚአብሔር አንድነት ስትለይ በመሆኑ፡- «አንቺ ነፍስ በሞት ምክንያት ከሥጋሽ እንደተለየሽ ሁሉ በኃጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር አንድነት ተለይተሽ ይሆን? ከእግዚአብሔርስ አንድነት አይለይሽ፤» ብሎ ስለ ነፍስ ማዘን፥ ማልቀስ ይገባል። አዳምና ሔዋንን «ሞቱ»  ያሰኛቸው ከእግዚአብሔር አንድነት መለየታቸው ነበር እንጂ የዕፀ በለስን ፍሬ እንደበሉ ወዲያው በመሞታቸው አይደለም ዘፍ ፫፥፰። አስቀድሞ የተነገራቸው «ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያሳየውና ከሚያስታውቀው ዛፍ አትበላ፤ ከእርሱ በበላህ ጊዜ ሞትን ትሞታለህና፤» የሚል ነበር። ዘፍ ፪፥፲፯። በአዲስ ኪዳንም ራሱ ባለቤቱ፡- ወደ እርሱ አንድነት ማለትም ቃለ ሕይወት ወንጌል ወደምትነገርበት ጉባኤ ያልመጡትን በቁማቸው ሙታን ብሏቸዋል። ማቴ ፰፥፳፪
፩፥፫፡- አስከሬን ከቤት ሲወጣ፤
          አስከሬን ከቤት በሚወጣበት ጊዜ፡- «አንተ ሰው፥ አንቺ ሰው በሞት ምክንያት ከምድራዊ ቤታችሁ እንደወጣችሁ ሁሉ በኃጢአት ምክንያት ከሰማይ ቤታችሁ ከመንግሥተ ሰማያት ትወጡ ይሆን? ይህንንስ አያድርግባችሁ፥ ከመንግሥተ ሰማያት አያውጣችሁ፤» ብሎ ማዘን፥ ማልቀስ ይገባል። «አምስቱ ውሾች ግን ከዚያች ሀገር ወደ ውጭ ይወጣሉ፤ እነዚህም አስማተኞች፥ ዘማውያን፥ ነፍሰ ገዳዮች፥ ጣዖት የሚያመልኩ፥ የሐሰት ሥራንም ሁሉ የሚወዱ ሁሉ ናቸው።» ይላል። ራእ ፳፪፥፲፭። ያች ሀገር መንግሥተ ሰማያት ናት። «የዚያን ጊዜም፡- ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ (እፈርድባቸዋለሁ)።» የሚልም አለ። ማቴ ፯፥፳፫።
፩፥፬፡- አስከሬን ወደ መቃብር ሲወርድ፤
          የተገነዘ አስከሬን ወደ መቃብር በሚወርድበት ጊዜ፡- «አንተ ሰው፥ አንቺ ሰው በሞት ምክንያት ወደ መቃብር እንደወረዳችሁ ሁሉ በኃጢአት ምክንያት ወደ ሲኦል ወደ ገሃነመ እሳት ትወርዱ ይሆን? ይኸንንስ አያድርግባችሁ፥ ወደ ሲኦል፥ ወደ ገሃነም አያውርዳችሁ፤» ብሎ ማዘን፥ ማለቀስ ይገባል። ምክንያቱም፡- «እናንተ የተረገማችሁ ለሰይጣንና ለመልእክተኞቹ ወደተዘጋጀው ወደ ዘለዓለም እሳት ሂዱ።» የሚል አለና ነው። ማቴ ፳፭፥፵፩ ከዚሀም አስቀድሞ «በወንድሙ ላይ በከንቱ የሚቆጣ ሁሉ እርሱ ይፈረድበታል ፤ ወንድሙንም ጨርቃም የሚለው ሁሉ የሸንጎ ፍርድ ይገባዋል ፤ ደንቆሮ የሚለውም ሁሉ የገሃነመ እሳት ፍርድ ይገባዋል።» ተብሎ ተነግሯል። ማቴ ፭፥፳፩። በቅዱስ ማርቆስ ወንጌል ደግሞ «እሳቱ የማይጠፉ ትሉ የማያንቀላፋ» የሚል ተጽፏል።
፪፡- የሚገባ ኀዘን፤
          ቅዱሳት መጻሕፍት በጠቅላላው የሚመክሩን የሚገባ ኀዘን እንድናዝን ነው። ጌታችንም የተናገረው ስለዚህኛው ኀዘን ነው። ነገ በነገር ሁሉ ደስ እንዲለን ዛሬ በፈቃዳችን እንድናዝን ነው። ይህም ቅዱሳንን፥ መላእክትን፥ እግዚአብሔርንም ደስ የሚያሰኝ ነው።
          «መጀመሪያ፡- በጻፍሁት መልእክት ባሳዝናችሁም እንኳ አይጸጽተኝም፤ ብጸጸትም፥ እነሆ ያች መልእክት ለጥቂት ጊዜ ብቻ እንዳሳዘነቻችሁ አያለሁ። አሁን ግን እኔ ስለ እርሷ በብዙ ደስ ይለኛል፤ ደስታዬም ስለ አዘናችሁ አይደለም፤ ንስሐ ልትገቡ ስለአዘናችሁ እንጂ፤» ፪ኛ ቆሮ ፯፥፰።
          «እላችኋለሁ፥ እንዲሁ ንስሐ ስለሚገባ ስለ አንድ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት በሰማያት ደስታ ይሆናል።» ሉቃ ፲፭፥፲።
          «እውነት እላችኋለሁ፤ ባገኘው ጊዜ ካልጠፉት ከዘጠና ዘጠኙ ይልቅ ጠፍቶ ስለተገኘው ፈጽሞ ደስ ይለዋል። እንዲሁም ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱ እንኳ ይጠፋ ዘንድ በሰማያት ባለው አባቴ ፊት አይፈቀድም።» ይላል። ማቴ ፲፫፥፲፫። የሚገባ ኀዘንን የምናዝነው ስለ አራት ነገር ነው። እነኚህም፡-
          ፪፥፩፡- የግል ኃጢአትን እያሰቡ ማዘን፤
መቅድመ ወንጌል፡- «አልቦቱ ካልእ ኅሊና ለአዳም ላዕለ ኃጢአቱ፥ ዘእንበለ ብካይ፤ አዳም በኃጢአቱ ምክንያት በመጣበት ብድራት ከማልቀስ በስተቀር ሌላ ኅሊና (አሳብ) አልነበረውም፤» እንዲል፥ በኃጢአቱ ምክንያት አለቀሰ። «ከማዕረጌ ተዋረድኩ፥ ከሥልጣኔ ተሻርኩ» ብሎ ሳይሆን ፈጣሪዬን በደልኩ ብሎ አዘነ። ይህ እንባ፥ ይህ ኃዘን ነው፥ «ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ፤» የሚል ተስፋ ያሰማው፤ የአዳም ኀዘኑ ፈጣሪን ከሰማይ እንዲወርድ፥ ከድንግል ማርያም እንዲወለድ፥ በቀራንዮ በመልዕልተ መስቀል ተሰቀሎ፥ አዳምን እስከነ ልጅ ልጆቹ እንዲያድን አድርጎታል።
          ንጉሠ እስራኤል ዳዊትም ስለ ድቀቱ በነቢየ እግዚአብሔር በተገሠጸ ጊዜ፦ «እግዚአብሔርን በድያለሁ፤» ብሎ አለቀሰ። በዚህን ጊዜ ነቢዩ ናታን፦ «እግዚአብሔር ደግሞ ኃጢአትህን አርቆልሃል፤ አትሞትም። ነገር ግን በዚህ ነገር ለእግዚአብሔር ጠላቶች ታላቅ የስድብ ምክንያት አድርገሃልና፤ ስለዚህ ደግሞ የተወለደልህ ልጅ ፈጽሞ ይሞታል፤» አለው። ፪ኛ ሳሙ ፲፪፥፲፫። ስምዖን ጴጥሮስም ጌታ አስቀድሞ እንደተናገረበት ዶሮ ሳይጮህ ሦስት ጊዜ ጌታውን አላውቀውም ብሎ ነበር። ይህንንም ያለው ከልቡ ሳይሆን ከአፉ ነው፤ ወዲያውኑ ዶሮ ጮኸ። ስምዖን ጴጥሮስም፡- «ዶሮ ሳይጮህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ፤» ያለው የኢየሱስ ቃል ትዝ አለው፤ ወደ ውጭም ወጥቶ መራራ ልቅሶ አለቀሰ። ማቴ ፳፮፥፴፫-፸፭። ሁሉም መልካቸው ሳይለወጥ፥ ሳይሰቀቁ ዕንባቸው እንደ ሰን ውኃ ይወርድ ነበር።
፪፥፪፡- የባልንጀራን ኃጢአት እያሰቡ ማዘን፤
          ነቢዩ ሳሙኤል ስለ ንጉሥ ሳኦል ኃጢአት በመዓልትም በሌሊትም ያለቅስ ነበር። እግዚአብሔርም ሳሙኤልን፡- «በእስራኤል ላይ እንዳይነግሥ ለናቅሁት ለሳኦል የምታለቅስለት እስከመቼ ነው?» ብሎታል። ፩ኛ ሳሙ ፲፮፥፩። በአዲስ ኪዳን ደግሞ ከሁሉም በላይ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡- ለኢየሩሳሌም አልቅሶላታል። «ሲቀርብም ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት። እንዲህም አላት፥አንቺስ ብታውቂ ሰላምሽ ዛሬ ነበር፤ ከእንግዲህ ወዲህ ግን ከዐይኖችሽ ተሰወረ። ጠላቶችሽ አንቺን የሚከቡበት ቀን ይመጣል፤ ይከትሙብሻል፤ ያስጨንቁሻልም፤ በአራቱ ማዕዘንም ከብበው ይይዙሻል። አንቺን ይጥሉሻል፤ ልጆችሽንም ከአንቺ ጋር ይጥሉአቸዋል፤ ድንጋይ በድንጋይ ላይ አይተዉልሽም፤ የይቅርታሽን ዘመን አላወቅሽምና፤» ይላል። ሉቃ ፲፱፥፵፩። በኦሪቱ የነቢያት አለቃ ሙሴ ስለ ወገኖቹ ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ፡- «አሁን ይህን ኃጢአታቸውን ይቅር በላቸው፤ ያለዚያ ግን ከጻፍከው መጽሐፍህ እባክህ ደምስሰኝ፤» ብሏል። ዘዳ ፴፪፥፴፪። ንጉሡ ዳዊትም የእግዚአብሔር መልአክ ከሕዝቡ ሰበዐ ሺህውን በቀሠፈ ጊዜ፡- «እነሆ፥ እኔ በድያለሁ፥ ጠማማም  ሥራ እኔ አድርጌአለሁ፤ እነዚህ በጎች ግን እነርሱ ምን አደረጉ? እጅህ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ እንድትሆን እለምንሃለሁ፤» ሲል ተናግሯል። ፪ኛ ሳሙ ፳፬፥፲፯። ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ፡- «ብዙ  ኀዘን የማያቋርጥም ጭንቀት በልቤ አለብኝ ስል በክርስቶስ ሆኜ እውነትን እናገራለሁ፤ አልዋሽምም፤ ሕሊናዬም በመንፈስ ቅዱስ ይመሰክርልኛል። በሥጋ ዘመዶቼ ስለሆኑ ስለ ወንድሞቼ ከክርስቶስ ተለይቼ እኔ ራሴ የተረገምሁ እንድሆን እጸልይ ነበርና፤» ብሏል። ሮሜ ፱፥፩።
፪፥፫፡- ግፍዓ ሰማዕታትን እያሰቡ ማዘን፤
          ቅዱስ እስጢፋኖስ ከጥንት ጀምሮ የነበረውን፥ የእምነት ሰዎች ታሪክ፥ ከአብርሃም ጀምሮ እየተረከ እውነቱን ቢነግራቸው አይሁድ ተበሳጩበት። ጥርሳቸውንም አፋጩበት። ቅዱስ እስጢፋኖስ ግን አድሮበት በሚኖር መንፈስ ቅዱስ ጸንቶ ወደ ሰማይ ቢመለከት ሥላሴን አየ። ያየውንም ምስጢር (ምሥጢረ ሥላሴን) ነገራቸው። እነርሱም በታላቅ ቃል ጮኸው እንዳይሰሙ ጆሮአቸውን ደፈኑ። መሬት ለመሬት እየጐተቱም ከከተማ አወጡት። በድንጋይም ቀጥቅጠው ገደሉት ፤ ደጋግ ሰዎችም አስክሬኑን አንስተው እያዘኑ እያለቀሱ ቀበሩት ይላል። የሐዋ ፰፥፪። ያሳዘናቸው፥ ያስለቀሳቸው ሞቱ ብቻ ሳይሆን የተፈጸመበት ግፍ ጭምር ነው። ስለሆነም ዓለም የግፈኞች በመሆኗ  ፍርድ ሲጓደል፥ ደሀ ሲበደል ቅዱሳን ሲገፉ ማዘን ይገባል።
፪፥፬፡- መከራ መስቀሉን እያሰቡ ማዘን፤
          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን በጥቅሉ አሥራ ሦስቱን ሕማማተ መስቀል ተቀብሏል። ይኸንን በተመለከተ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ፡- «ከኃጢአታችን ያወጣን ዘንድ፥ በጽድቁም ያድነን ዘንድ፥ እርሱ ስለ ኃጢአታችን በሥጋው በእንጨት ላይ ተሰቀለ፤ በግርፋቱም ቁስል ቁስላችሁን ተፈወሳችሁ።» ብሏል። ፩ኛ ጴጥ ፪፥፳፬። ይህም ነቢዩ ኢሳያይስ፡- «እርሱ ግን በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፤ ሕመማችንንም ተሸከመ፤ ስለ እኛም ታመመ፤--- እርሱ ግን ስለ ኃጢአታችን ቈሰለ፤ ስለ በደላችንም ታመመ፤--- በእርሱም ቁስል እኛ ተፈወስን።» በማለት አስቀድሞ የተናገረው ነው። ኢሳ ፶፫፥፬። በመሆኑም ስለ እኛ ብሎ የተቀበላቸውን እነዚህን መከራዎች እያሰብን ልናዝን ይገባል። ቅዱስ ዮሐንስ የዕለተ ዓርቡን መከራ በቀራንዮ ፊት ለፊት በማየቱ ሰበዓ ዘመን ቁጽረ ገጽ (ኀዘንተኛ) ሁኖ ኑሯል። መላ ዘመኑን በፊቱ ላይ ፈገግታ አልታየም።
ለመሆኑ የእኛ ኀዘን ምን ይመስላል?
          ከደስታ በቀር ሐዘንን የምንፈልግ ሰዎች አይደለንም። ማናችንም ብንሆን ቢሳካልን ለአንድ ደቂቃ እንኳን ማዘን አንፈልግም። ቢቻለን የዓይን አምሮታችን የሥጋ ፍላጐታችን ሁሉ ተሟልቶልን በዓለም ተደስተን መኖርን እንፈልጋለን። ይልቁንም ስለ ኃጢአታችን ፈጽሞ ማዘን አንፈልግም። እንዲያውም እንደ ኃጢአት የሚያስደስተን ነገር የለም። ያመነዘሩበትን፥ ጠጥተው የሰከሩበትን፥ አጭበርብረው ብዙ ገንዘብ ያገኙበትን፥ በጭፈራ ያሳለፉበትን፥ የጠሉትን ሰው የተበቀሉበትን፥ በአጠቃላይ በተለያየ መንገድ ሰውን የጐዱበትን ዕለትና ዘመን እያስታወሱ የሚደሰቱ ፥ ሐሴትም የሚያደርጉ ሰዎች እጅግ ብዙ ፥የብዙ ብዙ ናቸው። የሰው ሕይወት በሥጋዊውም ሆነ በመንፈሳዊው ሲመሰቃቀል፥ የሰው ትዳር ሲበጠበጥ ፥ ሲፈርስ ፥ በደስታ ያልተሳሉትን ስእለት ለማስገባት የሚፈልጉ ሰዎችም አይጠፉም። ሰው ሲታመም፥ ሥራም ሲፈታ አንጀታቸው ቅቤ የሚጠጣ ፈጽመው የሉም ለማለት አይቻልም። ወተቱን አጥቁረው፥ ማሩንም አምርረው ሰውን በማማት የሰውንም ስም በማጥፋት መደሰት እንደ ዘውትር ጸሎት የተያዘ የየዕለቱ ግብር ነው። የእጅ ስልካችን፥ የቤታችንም ስልክ፥ ኢ-ሜይላችንም ጭምር የሚያሳብቀው ይኸንኑ ነው። ይህ ሁሉ ከራስ ወዳድነት (ራስን ከማምለክ) የሚመነጭ ነው። «ነገር ግን በኋላ ዘመን ክፉ ጊዜ እንደሚመጣ ይህን ዕወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፥ ገንዘብንም የሚወዱ፥ ቀባጣሪዎች፥ ትምክሀተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ ምስጋና የሌላቸው፥ ከጽድቅም የወጡ ይሆናሉ። ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተነፉ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ።» እንዳለ ሐዋርያ። ፪ኛ ጢሞ ፫፥፩።
          ምናልባት የምናዝነው ያሰብነውና ያቀድነው፥ ኃጢአት ሳይሳካልን ሲቀር ነው። ወይም የገፋነው ሰው ሳይወድቅ ሲቀር፥ ያዋረድነው ሰው ሲከብር፥ ያቆሰልነው ሰው ሲፈወስ፥ ያጠመድነውና ያስጠመድነው ሰው ከወጥመድ ሲያመልጥ፥ የጠላነው ያስጠላነው ሰው ሲወደድ፥ ቤት መኪና ያልነበረው ሰው እንደ እኛ ባለቤት ባለ መኪና ሲሆን ፥ በውጭው ዓለም የመኖሪያ ፈቃድ አጥቶ የተቸገረ ሰው እንደ እኛ መኖሪያ ፈቃድ ሲያገኝ፥ እንረዳው የነበረ ሰው ራሱን ሲችል ነው። የኰንትሮባንድ ነጋዴ የሚበሳጨውና የሚያዝነው ኬላ ላይ የእርሱ ተይዞ ስለተወረሰበት ሳይሆን የባልንጀሮቹ በተለያየ ምክንያት ሳይወረስ በመቅረቱ ነው። በአጠቃላይ አነጋገር በኃጢአታችንና እና በሰው ጉዳት የምንደሰት ሰዎች ነን። መመሪያችን እኔ ልደሰት ፥ ልሳቅ ፥ ይድላኝ ፤ ሌላው ግን ይዘን፥ ያልቅስ፥ ይጐስቁል ነው። እኔ ወርቅ ልልበስ ፥ ሌላው ግን አፈር ይልበስ ነው። ለአንድ አፍታ እንኳን ምድራዊው ነገር ሁሉ ሃላፊ ጠፊ መሆኑ ትዝ አይለንም። «ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢገዛ፥ ነፍሱንም ቢያጣ፥ ለሰው ምን ይረባዋል?» የሚለውን የጌታችንን ቃል የምናውቀው በጥቅስ ብቻ ነው። ማቴ ፲፯፥፳፮። ከእንግዲህ ግን እንደቃሉ ለመኖር እንጣር። እኛ ጥቂት ስንጥር እግዚአብሔር በብዙ ይረዳናል። እንደ ራሄል ወደ ሰማይ የሚወጣ እንባ ይሰጠናል። ኀዘናችን ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶ ግዳጅ የሚፈጽም ይሆናል። የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን አሜን።

13 comments:

 1. Fetsume netuh kale!! Kale Hiwot Yasemalen!!

  ReplyDelete
 2. Amen, Kale Hiwot Yasemalin

  ReplyDelete
 3. አሜን። አባታችን ቃለ ህይወት ያሰማልን፤ መንግስተ ሰማያትን ያውርስልን።

  ReplyDelete
 4. egeziabeher ken lebona yeseten kale heyewet yasemalegn

  ReplyDelete
 5. betam des yemil kale Egziabier new. tsegawun yabzalot,kihnetotin yibarkilot kesis. kale hiwot yasemalin

  ReplyDelete
 6. kalehiwot yasemalen

  ReplyDelete
 7. ልብን ሰርስሮ የሚገባ ትምህርት ነው ቃለ ህይወት ያሰማልን

  ReplyDelete
 8. kale hiyowt yasemalin

  ReplyDelete
 9. amen abatachin kale hiwot yasemalin

  ReplyDelete
 10. kalehiwot yasemalin

  ReplyDelete
 11. Kale hiwot yasemalin!

  ReplyDelete