Sunday, November 14, 2010

ነገረ ማርያም ክፍል ፫

፯ «ዳግመኛ በሰማይ ሌላ ምልክት ታየ፤»

«ወአስተርአየ ካልእ ተአምር በውስተ ሰማይ፤» ቅዱስ ዮሐንስ የመጀመሪያውን ምልክት ፦ ታላቅ ፥ ገናና ፥ ደገኛ ካለ በኋላ የሁለተኛውን ግን ቀለል አድርጐ « ሌላ ምልክት በሰማይ ታየ ፤» ብሏል።
፯ ፥ ፩ ታላቅ ቀይ ዘንዶ፤
ይኸውም፦  « አርዌ ዐቢይ ወቀይሕ ፤» እንዲል፦ እሳት የሚመስል ቀይ ዘንዶ ነው። ሰባት ራሶችና ዐሥር ቀንዶችም ነበሩት፤ በራሶቹም ላይ ሰባት ዘውዶች ነበሩት። ዘንዶ (እባብ) የተባለውም ፦ የቀደመ ሰው አዳምን፦ እግዚአብሔርን ያህል አባት ፥ ገነትን ያህል ርስት ያሳጣው ጥንተ ጠላታችን ዲያቢሎስ ነው። ምክንያቱም በሥጋ ከይሲ ተሰውሮ አዳምንም ሔዋንንም አስቷቸዋልና። « እባብም እግዚአብሔር አምላክ ከፈጠራቸው ከምድር አራዊት ሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ ነበር ፤ » ይላልና። ዘፍ ፫ ፥፩። እሳት የሚመስል ቀይ መባሉም ተፈጥሮው ልክ እንደ ሌሎቹ መላእክት ከእሳትና ከነፋስ በመሆኑ ነው። ይኽንንም ቅዱስ ዳዊት ፦ «መላእክቱን መንፈስ ፥ አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል የሚያደርጋቸው።» በማለት ገልጦታል።መዝ ፩፻፫ ፥ ፬። ይህም እሳትና ነፋስ ኃያላን ፥ ረቂቃን እንደሆኑ ሁሉ መላእ ክትም፦ ኃያላን ፥ ረቂቃን ፥ ፈጣኖች ፥ ፈጻሚያነ መፍቅድ ናቸው ፥ ለማለት ነው።
፰ ፥ ሰባት ራሶች፤
ሰባት በዕብራዊያን ፍጹም ቁጥር ነው። ዲያቢሎስም ፍጹም ኃጢአትን ያሠራል። ሰባት ራሶች የተባሉትም ሰባቱ አርዕስተ ኃጣውእ (ዋና ዋና ኃጢአቶች ) ናቸው። እነዚህን ዋና የተባሉትን ፥ ከእግዚአብሔር አንድነት የሚለዩትን ፥ ከክብሩም የሚያርቁትን ኃጢአቶች በሰው አድሮ ያሠራው ሲያሠራም የሚኖረው እርሱ ነው።
፰፥፩፦ ኃጢአተ አዳም፤
«እባብም ለሴቲቱ ፦ ሞትን አትሞቱም ፤ ከእርሷ በበላችሁ ቀን ፥ ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ ፥ እንደ እግዚአብሔርም እንደምትሆኑ ፥ መልካምንና ክፉን እንደምታውቁ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ።» አላት። ዘፍ ፫፥፬። አዳምና ሔዋን በዚህ ምክር የሰባት ዓመት ንጽሕናቸውን አቆሸሹ ፥ ቅድስናቸውን አረከሱ፤ ከማዕረጋቸው ተዋረዱ ፥ ከሥልጣናቸው ተሻሩ ፥ ከገነት ተባረሩ። ዘፍ ፫ ፥ ፲፬።
፰፥፪ ፦ ቅትለተ አቤል፤
አዳም አቤልን «ይህ ብሩኅ ገጽ ያለው ልጄ መንግሥቴን የሚወርሰው እርሱ ነው፤» ይለው ነበር። ሁለተኛም ከቃየል ጋር መንታ ሆና የተወለደችውን መልከ መልካም አጋባው። ሦስተኛም አቤል ከበጐቹ በኲራት ፥ ቀንዱ ያልከረከረውን ፥ ጠጉሩ ያላረረውን ፥ጥፍሩ ያልዘረዘረውን ጠቦት መሥዋዕት እድርጐ ቢያቀርብ እግዚአብሔር ተቀበለው። በዚህ ሁሉ ምክንያት ቃየል ተበሳጨ። ልቡ አዘነ ፥ ፊቱ ጠቆረ። በዚህን ጊዜ ሰይጣን አዛኝ መስሎ ቀርቦ ነፍስ መግደልን ለቃየል አስተማረው። አንዱ ሰይጣን በሰው አምሳል ሁለተኛው ደግሞ በቊራ አምሳል ለቃየል ታዩት። በሰው አምሳል የታየው በቊራ አምሳል የታየውን በደንጊያ ሲገድለውም አየ። ከዚህ በኋላ ነው ወንድሙን አቤልን የገደለው። ዘፍ ፬፥፩-፰።
፰፥፫፦ ጥቅመ ሰናዖር ፤
የዓለም ሁሉ ቋንቋ አንድ ፥ ንግግሩም አንድ ነበር። ሰይጣን ልባቸውን አነሣሥቶት ጫፉ ሰማይ የሚደርስ ግንብ ለመሥራት በሰናዖር ሜዳ ተሰባሰቡ። ይኸውም ስለ ሁለት ነገር ነው። አንደኛው ፦ እንደ ኖኅ ዘመን የጥፋት ውኃ ቢመጣ ማምለጫ እንዲሆናቸው ነው። ሁለተኛው ደግሞ እግዚአብሔርን ለመውጋት ነው። በመጽሐፈ ኲፋሌ እንደ ተጻፈው አርባ ሦስት ዓመት ፈጅቶባቸዋል። ከዚህ በኋላ ፍላፃቸውን ወደ ላይ ቢወረውሩት በአየር ላይ ያሉ አጋንንት በምትሀት ደም እየቀቡ ይሰዱላቸው ነበር። አሁን ገና ባለቤቱን ወጋነው፥ ቀኝ አዝማቹን ፣ ግራ አዝማቹን ወጋነው ፥ አጋፋሪውን ወጋነው ይባባሉ ጀመር። ሥላሴ ፍጥረቱ ሁሉ በከንቱ ቢጐዳ አይወዱምና ለኃጢአት እንዳይግባቡ ሰባ ሁለት ቋንቋ አመጡባቸው። እነርሱም በምንም መግባባት ስላልቻሉ ትተውት ወረዱ። ግንቡንም ጣዖት አድርገው እንዳያመልኩት ሥላሴ ጽኑ ነፋስ አስነሥተው በትነውታል። በዚህም ምክንያት ባቢሎን ተብሎአል። ባቢሎን ማለት ዝርው (የተበተነ) ማለት ነው። አንድም ሕዝቡ በቋንቋ ፥ በነገር ተለያይተው በቦታ ስለተበተኑበት ባቢሎን ተብሏል። በዚህን ጊዜ ቋንቋ ከሦስት ተከፍሏል። ሠላሳ ሁለቱ በነገደ ካም ፥ ሃያ አምስቱ በነገደ ያፌት ፥ አሥራ አምስቱ በነገደ ሴም ቀርቷል።
፰፥፬ ፦ ኃጢአተ ሰዶም፤
          የሰዶማውያን ኃጢአታቸው ወንድ ከወንድ ፥ ሴት ከሴት መጋባታቸው ነው። ይኽንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ፦ «ስለዚህም እግዚአብሔር ክፉ መቅሠፍትን አመጣባቸው ፤ ሴቶቻቸውም ለባሕርያቸው የሚገባቸውን ትተው ለባሕርያቸው የማይገባውን ሠሩ። ወንዶችም እንዲሁ ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን ትተው በፍትወት ተቃጠሉ፤ እርስ በራሳቸውም እየተመላለሱ ፥ ወንዶች በወንዶች ላይ የሚያዋርዳቸውን ነውር ሠሩ፤ ነገር ግን ፍጻሜአቸውን ያገኛሉ፤ ፍዳቸውን ያገኛሉ፤ ፍዳቸውም በራሳቸው ይመለሳል።» በማለት ገልጦታል። ሮሜ ፩፥፳፮። «የአምላክህንም ስም አታርክስ ፥ እኔ እግዚአብሔር ነኝ ፤ ከሴትም ጋር እንደምትተኛ ከወንድ ጋር አትተኛ ፤ ጸያፍ ነገር ነውና።» የሚለውን አስቀድሞ በሕገ ልቡና የተሰጣቸውን ሕግ ተላለፉ። ዘሌ ፲፰፥፳፪። እግዚአብሔርም በሰዶምና በገሞራ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ከሰማይ እሳትና ዲን አዘነበ፤ እነዚያም ከተሞች በዙሪያቸው ያለውንም ሁሉ ፥ በከተሞችም የሚኖሩትን ሁሉ ፥ የምድርንም ቡቃያ ሁሉ ገለበጠ። አብርሃምም ወደ ሰዶምና ገሞራ ወደ አውራጃዎቿም ሁሉ ተመለከተ ፤ እነሆም፥ ነበልባል ከምድር እንደ ምድጃ ጢስ ሲወጣ አየ ይላል። ዘፍ ፲፱፥፳፫።
፰፥፭፦ ኃጢአተ እሥራኤል፤
የእሥራኤል ኃጢአት ከአምልኮተ እግዚአብሔር ወደ አምልኮተ ጣዖት ማፈግፈግ ነበር። እግዚአብሔር ከባርነት ቤት ካወጣቸው በኋላ በሲና ምድር በዳ የወርቅ ጥጃ ሠርተው በማምለክ አሳዝነውታል። ዘጸ ፴፪፥፬። ከሞአብ ልጆች ጋር ባመነዘሩም ጊዜ ብዔልፌጎር የተባለውን ጣዖት ተከትለው ነበር። ዘኁ ፳፭፥፩። ብዙ ጊዜ የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ትተው በዙሪያቸው ያሉ አሕዛብን አማልክት በመከተል በመስገድም እግዚአብሔርን አስቆጥተውታል። እርሱም ለጠላቶቻቸው እያሳለፈ ይሰጣቸው ነበር። መሳ ፪፥፲፩ ፣ ፪ኛ ነገ ፲፯፥፯ ፣፳፩፥፲፩። በአጠቃላይ አነጋገር ጣዖትን ማምለክ የአጋንንት ማኅበርተኛ መሆን ነው። ፩ኛ ቆሮ ፲፥፳ ።
፰፥፮፦ ቅትለተ ዘካርያስ፤
ካህኑ ዘካርያስ ከሚስቱ ከኤልሳቤጥ ጋር በእግዚአብሔር ሥርዓትና በትእዛዙም ሁሉ ያለ ነውር የሚሄዱ ጻድቃን ነበሩ። ሉቃ ፩፥፮። ዘመን ከተላለፋቸው በኋላ በዕርግና ፥ በቅዱስ ገብርኤል ብሥራት መጥምቀ መለኰት ቅዱስ ዮሐንስን ወለዱ። ሉቃ ፩፥፰ ፣ ፶፯። ጌታ በወንጌል እንደተናገረ ዘካርያስን በቤተ መቅደሱና  በመሠዊያው መካከል እንዳለ ገድለውታል። ማቴ ፳፫፥፴፭። የዘካርያስም ደም ሰበዓ ዘመን ሙሉ ሲፈላ እንደ አቤል ደም ሲካሰስ ኖሯል። ታሪኩ እንዲህ ነው። ለአንድ ዓላዊ ፦ ሲፀነስ የአባቱን አንደበት የዘጋ ፥ ሲወለድ የከፈተ አንድ ሕፃን ከካህኑ ከዘካርያስ ቤት አለልህ አሉት። እርሱም ዘካርያስን አስጠርቶ ቢጠይቀው፦ «አዎን አለ፥ምነው ጠየቅኸኝ?» አለው። ዓላዊውም «ይኽንኑ እንድትነግረኝ ነው ፥ በል ሂድ ፤» ሲል መለሰለት። በዚህን ጊዜ ዘካርያስ «ይህ ዓላዊ ያለ ምክንያት አልጠየቀኝም ፤ ሀብት ሳላሳድርበት ልጄን ሊያስገድለው ነው።» ብሎ ከቤተ መቅደስ አግብቶ ሲጸልይለት ዓላዊው «ልጁን ግደሉ፤» ብሎ ጭፍራ ላከ። ከቤት ቢሄዱ አጡት። ወዲያው የእግዚአብሔር መልአክ ለኤልሳቤጥ ተገለጠላትና ፦ ይህ ዓላዊ ልጅሽን ሊያስገድልብሽ ነውና ፥ ወደ ገዳም (በረሀ) ይዘሽው ሂጂ ፤» አላት። እርሷም ልጁን ከዘካርያስ ተቀብላ የተባለችውን አድርጋለች። በመጨረሻም የተላኩት ጭፍሮች ወደ ቤተ መቅደስ ቢሄዱ ዘካርያስን አግኝተው ገድለውታል።
፰፥፯ ፦ ሞተ ወልደ እግዚአብሔር፤
በአይሁድ ልቡና አድሮ ፥ እንዳይሰሙ ፥እንዳይለሙ አዕምሮአቸውን አሳውሮ ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስን ያስገረፈ ያሰቀለ ሰይጣን ነው። ሥጋው አልቆ አጥንቱ እስኪቆጠር ድረስ ሰድስት ሺህ ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ጅራፍ ገርፈውታል። ራስ ራሱን በዘንግ ቀጥቅጠውታል። ይኽም አልበቃ ብሎ ልቡ ድረስ እስኪሰማው አክሊለ ሦክ ደፍተውበታል። እጆቹን የኋሊት አስረውታል። በጥፊ መትተውታል ፥ አክታቸውን ተፍተውበታል ( ከብርሃናዊ ፊቱ ላይ ለጥፈውበታል )። ከባድ መስቀል አሸክመውታል ፥ ከምድር ላይ አዳፍተውታል። ሳዶር ፥ አላዶር ፥ ዳናት ፥አዴራ ፥ ሮዳስ በተባሉ አምስት ቀኖት ቸንክረውታል። መራራ ሐሞት አጠጥተውታል ፥ ጐኑን በጦር ወግተውታል። በመጨረሻም «ተፈጸመ፤» በማለት በፈቃዱ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቷል። ዮሐ ፲፱ ፥፴።
፱፦ አሥር ቀንዶች፤
ቀንድ በምሳሌነት፦ ኃይልን ፥ ክብርን ፥ ሥልጣንን ፥ ንግሥናን ያመለክታል።
-       «እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እስኪጠፉ ድረስ በእነዚህ ቀንዶች ሶርያውያንን ትወጋቸዋለህ።» ፩ኛ ነገ ፳፪፥፲፩።
-       «ሐናም ጸለየች፤ እንዲህም አለች፦ ልቤ በእግዚአብሔር ጸና፤ ቀንዴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ከፍ ከፍ አለ።» ፩ኛ ሳሙ ፪፥፩
-       «ለንጉሦቻችንም ኃይልን ይሰጣል፤ የመሲሑንም ቀንድ ከፍ ከፍ ያደርጋል።» ፩ኛ ሳሙ ፪፥፩።
-       «በዚያ ለዳዊት ቀንድን አበቅላለሁ፤» መዝ ፩፻፴፩ ፥ ፲፯።
-       «በዚያ ቀን ለእሥራኤል ቤት ቀንድን አበቅላለሁ፤» ሕዝ ፳፱፥፳፩።
እነዚህ ሁሉ ለፍጻሜው ለኢየሱስ ክርስቶስ የተነገሩ ናቸው። ይኽንንም ጻድቁ ካህን ዘካርያስ አድሮበት የሚኖር መንፈስ ቅዱስ ምሥጢሩን ፥ ጥበቡን ቢገልጥለት፦ «ይቅር ያለን ፥ ለወገኖቹም ድኅነትን ያደረገ የእሥራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን ፤ ከባርያው ከዳዊት ቤት የምንድንበትን ቀንድ አስነሣልን ፤ ከጥንት ጀምሮ በነበሩ በቅዱሳን ነቢያት አፍ እንደተናገረ። ከጠላቶቻችን እጅ ከሚጠሉንም ሁሉ እጅ ያድነን ዘንድ። ቸርነቱን ከአባቶቻችን ጋር ያደርግ ዘንድ ፥ ቅዱስ ኪዳኑንም ያስብ ዘንድ። ለአባታችን ለአብርሃም የማለውን መሓላ ያስብ ዘንድ።» በማለት ተናግሯል። ሉቃ ፩፥፷፯።
፱ ፥ ፩፦ የሳጥናኤል ውድቀት፤
ሰይጣን በክህደቱ አጥቶት እንጂ ክብርም ፥ ኃይልም ሥልጣንም ነበረው። በአሥሩ የመላእክት ከተሞች በተሾሙ አሥር የመላእክት አለቆች ላይ የአለቃ አለቃ ነበር። የተፈጠረው የመላእክት አለቃ ሆኖ ነው። ይኽንንም ቀሌምንጦስ ተናግሮታል። እግዚአብሔር መላእክትን በነገድ መቶ ፥ በከተማ አሥር አድርጐ ፈጥሮ ተሰወራቸው። ይህም ካልፈለጉኝ አልገኝም ፥ ባሕርዬም አይመረምርም ሲላቸው ነው። ወዲያው፦ «እኛ ምንድር ነን? ከየት መጣን ? ማንስ ፈጠረን? በራስ በራሳችን ተፈጠርን ? ወይስ ከሌላ ነው?» አሉ። ዲያቢሎስ ከበታቹ እንዲህ ሲሉ ሰማ። ከበላዩ ደግሞ «ፈጠርኳችሁ፤» የሚል አጣ። በቦታው ከሁሉ በላይ አድርጎ ፈጥሮት ነበርና «እኔ ፈጠርሁ፤» ብሎ አሰበ ፥ አስቦም አልቀረ «እኔ ፈጠርኋችሁ፤» አለ። ይኽን ሰምተው «ሰጊድ ይገባዋል፤» ያሉ አሉ። «እኛም እንደ እርሱ ነን፤» ያሉም አሉ። « አምላክ ነኝ ያለስ ከእርሱ በቀር ሌላ የለምና ፥ ይሆንን?» ብለው የተጠራጠሩ አሉ። ሀልዎተ እግዚአብሔርን ሳይመረምሩ የቀሩም አሉ። እኲሌቶቹ ግን ፦ «በምን ፈጠርኋችሁ ይለናል። በቦታ ከበላይ በመሆን ፈጠርኋችሁ እንዳይለን ፥ እኛ የበታቾቻችንን መቼ ፈጠርናቸውና ነው?። በዚያውስ ላይ ምቀኞቹ አይደለንም፤ በእውነት ፈጣሪ ከሆነ ፈጥሮ ያሳየን ።» ብለው፦ «ፈጥረህ አሳየን፤» አሉት። እርሱም  እፈጥራለሁ ብሎ ፥ እጁን ወደ እሳት ቢጨምር ፈጀውና  « ዋይ» አለ። በዚህን ጊዜ «በአፍአ ያለውን (የሚነገረውንና እና የሚሠራውን ብቻ የሚያውቅ) አምላክ ቢሆን ነው እንጂ ውሳጣዊውን (ልብ ያሰበውን የሚያውቅ) አምላክ ቢሆን ኖሮ ገና ሳስበው ለምን አሰብከው ፥ «ባለኝ ነበር ፤» አለ።  ወዲያው ልቡን ተሰማውና «ዋይ» አለ። እግዚአብሔር ግን ፈወሰው። ይህንንም ማድረጉ ንስሐ ቢገባ እንደሚምረው ሲነግረው ነበር።
          ከዚህ በኋላ በመላእክት ሽብር ቢጸናባቸው፦ መልአከ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል፦ «ንቁም በበህላዌነ እስከ ንረክቦ ለአምላክነ ፤ አምላካችንን እስክናገኘው ድረስ በየህልውናችን ጸንተን እንቁም ፤» በማለት አጽንቷቸዋል። ይህም በጎ አርበኛ ጦር በተፈታ ጊዜ «አይዞህ ባለህበት ጽና፤» ብሎ እንደሚያጸናው ማለት ነው።« ወበእንተዝ ደለዎ ይፁር ዜናሃ ለማርያም ፤ በዚህ ምክንያት የድንግል ማርያምን ዜና ያደርስ ፥ ብሥራቷን ይናገር ዘንድ ተገባው ፤ » እንዲል ፥  ብሥራት ተሰጥቶታል። «በስድስተኛው ወር (አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ፥ ስድስተኛው ሺህ ደግሞ ሲጀምር) መልአኩ ገብርኤል . . .   ወደ አንዲት ድንግል ተላከ» ይላል። ሉቃ ፩፥፳፮።
እግዚአብሔርም ጨርሶ ሳያስታቸው ብሎ እርሱ (ሳጥናኤል) በሌለበት በኲል በምሥራቅ ባሕረ ብርሃንን አፍስሶላቸዋል። ከዚህም ጋር ስሙ የተጻፈበት መጽሔተ ብርሃን ቢሰጣቸው አንድነቱ ሦስትነቱ(ምሥጢረ ሥላሴ) ተገልጦላቸው « አሐዱ አብ ቅዱስ ፥ አሐዱ ወልድ ቅዱስ ፥ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ፤» ብለው አመስግነውታል። እርሱን ግን ባደረው ጨለማ ጠቅልሎ በዕለተ እሑድ  ከኢየሩሳሌም ሰማያዊት ወደ ኢዮር አውርዶታል።ከሰባቱ ሰማያት ሦስቱ ፦ ኢዮር ፥ራማ፥ኤረር የመላእክት ናቸው። በውስጣቸውም አስር የመላእክት ከተሞች አሉ። በእነርሱም ላይ አስር አለቆች ተሹመዋል። እግዚአብሔር ሳጥናኤል በሌለበት በኲል ባሕረ ብርሃንን ያፈሰሰላቸው «እኔ ፈጠርኩ » እንዳይል ነው።
ሳጥናኤል በኢዮር ሆኖ በዕለተ ሠሉስ የተፈጠሩ ዕፅዋት፥ አዝርዕት ፥ አትክልት ፥ጽጌያትን አይቶ እንዳያደንቅ፦ «እንዲህ አድርጐ አከናውኖ የፈጠረለት ቢኖር ነው፥ » አለ። እግዚአብሐርም «ከወደድሃት በዚያ ላኑርህ ፤» ቢለው «ደገኛይቱን ማን ከልክሎኝ ፤» አለ። ከዚህ በኋላ ለሚካኤልና ለገብርኤል «እናንተ ኢየሩሳሌም ሰማያት ይሏችኋል ፥ ሰባቱ ሰማያት እንኳ አያህሏትም። እኛ ከጩኸት በቀር የተጠቀምነው የለም። ገዢ ነኝ የሚለውን ወግተን እጅ እናድርግ።» ብሎ ላከባቸው። እነርሱም የተላኩትን ከንጉሥ ከተማ እንደገባ ዕብድ ውሻ አድርገው ሰደዷቸው። ተመልሰውም አልተቀበሉንም ቢሉት ፦ «ቀለምጺጸ እሳት (የእሳት ፍንጣሪ) የሆኑ ሚካኤል ገብርኤል በእኔ ዘንድ ምን ቁም ነገር ናቸው። ይልቁንስ ኑ ተሸከሙኝና እንሂድ ፤» አላቸው። በዚህን ጊዜ በአርባዕቱ እንስሳ (በኪሩቤል) አምሳል አራት ሁነው ተሸክመውት ሽቅብ እወጣለሁ ቢል ኃይል ተነሥቶታል። ወደ ታች እንጂ ወደ ላይ መውጣት የማይቻለው በመሆኑም ፦ «ጐየ እግዚእ ምስለ አርያሙ፤ እግዚአብሔር ሰማዩን (ጽርሐ አርያምን) ጠቅልሎ ሸሸ፤» ብሎ ተመለሰ።
ቅዱሳን መላእክት ግን ፍጥረትን ሲፈጥር እያዩ ያመሰግኑ ነበር። በዕለተ ረቡዕ  ፀሐይ ፥ ከዋክብት ፥ ጨረቃ ፥ ሲፈጠሩ አይተው አመስግነው አመስግን ቢሉት ፦ «አንሰ ዕድው (ውፁዕ) እምዝንቱ ኅሊና፤» እንዲል፦ «እኔ ከዚህ ውጪ ነኝ ፥ ባይሆን አራተኛ አድርጋችሁ ብታመሰግኑኝ እወዳለሁ፤» አላቸው። እነርሱም «ይህ ስሑት ፍጥረት እንዲህ እያለ እስከ መቼ ሲታበይ ይኖራል?» ብለው ሄደው ቢገጥሙት ድል አደረጋቸው። ሁለተኛም ቢገጥሙት ዳግመኛ ድል አደረጋቸው። በዚህን ጊዜ፦ «እኛስ ለአምላክነትህ ቀንተን ነበረ ፥ አንተ ግን ፈቃድህ ሳይሆን ቀረ፤» ብለው ወደ እግዚአብሔር ቢያመለክቱ ፦ «ፈቃዳችሁ ፈቃዴ ነው ፥ ነገር ግን ድል የሚነሣበትን (የሚሸነፍበትን) ታውቁ ዘንድ ነው፤» ብሎ ስሙ የተጻፈበትን ትእምርተ መስቀል ሰጣቸው። ያን ይዘው በዕለተ ረቡዕ ወደዚህ ዓለም አውርደውታል። በዚህን ጊዜ የእርሱ ወገኖች ለሦስት ተከፍለዋል። ሀለዎተ እግዚአብሔርን ሳይመረምሩ የቀሩ በአየር ቀርተዋል። ይሆን ፥ አይሆን ብለው የተጠራጠሩ በዚህ ዓለም ቀርተዋል። « አምላክ ነው ፥ ሰጊድ ይገባዋል፤» ያሉ አብረው እንጦሮጦስ ወርደዋል።


«ዘንዶውም በወለደች ጊዜ ልጅዋን ሊበላ በዚያች ሴት ፊት አንጻር ቆመ፡፡» . . . .  .  .

2 comments:

  1. i appreciate that, i hope it will be published in books so that every body will have access on this pure orthodoxy teaching.
    thanks.

    ReplyDelete
  2. አዎ አባታችን ወንድሜ/እህቴ ያቀረበውን ሀሳብ እኔም እጋራለሁኝ ወደመጽሐፍ ቢቀየር ብዙዎች የቃሉ ተካፋይ ይሁናል ብዙጊዜ ኢንተርኔት የማይጠቀሙ በብዛት ይኖራሉና፡፡ እርሶን ቃለህይወት ያሰማልን፡፡

    ReplyDelete