Saturday, November 6, 2010

ነገረ ቅዱሳን (ክፍል፫)


                                   ፭ ቤተመቅደስ

          አምልኮተ እግዚአብሔር የሚፈጸምበት የእግዚአብሔር ቤት ቅዱስ ነው። ይኸውም በሰማይ ባለ ቤተ መቅደስ አምሳል የተሠራ ነው። እግዚአብሔር ደብረ ሲናን በእሳት መጋረጃ ጋርዶ ለሙሴ ሰማይን ከፍቶ (ምሥጢር ገልጦ) ካሳየው በኋላ፦ «መቅደ ስ ትሠራልኛለህ፥ በመካከላችሁም አድራለሁ። በተራራው እንዳሳየሁህ ሁሉ፥ እንደማደሪያው ምሳሌ፥ እንደ ዕቃውም ሁሉ ምሳሌ ለእኔ ትሠራለህ፤ እንዲሁ ትሠራለህ።» ብሎታል። ዘጸ ፳፭፥፲።

          ፭፥፩፦ ደብተራ ኦሪት፤
 
እግዚአብሔር መንፈሱን በባስልኤልና በኤልያብ አሳድሮ ማስተዋልን ዕውቀትንና ጥበብን ሰጥቷቸው ደብተራ ኦሪትን ሠርተዋል ዘጸ ፴፩፥፩-፲፩። ይህ የድንኳን ቤተ መቅደስ የተቀደሰ የቅብዐት ዘይት ተቀብቶ ቅዱስ እንደሚሆንም አስቀድሞ ለሙሴ የነገረው እግዚአብሔር ነው። ዘጸ ፴፥፳፮። ይህም ይታወቅ ዘንድ ታቦት ባለበት በዚህ ቅዱስ ስፍራ እግዚአብሔር በደመና ዓመድ ይገለጥ ነበር። ሙሴም ወደ ድንኳን በገባ ጊዜ ዓምደ ደመና ይወርድ ነበር፤ እግዚአብሔርም ሙሴን ይናገረው ነበር። ሕዝቡም ሁሉ ዐምደ ደመናው በድንኳኑ ደጃፍ ሲቆም ያየው ነበር፤ ሕዝቡም ሁሉ ተነሥቶ እያንዳንዱ በድንኳኑ ደጃፍ ይሰግድ ነበር፤ እግዚአብሔርም፥ ሰው ከባልንጀራው ጋር እንደሚነጋገር ፊት ለፊት ከሙሴ ጋር ይነጋገር ነበር። ዘጸ ፴፫፥፯-፲፩።

፭፥፪፦ ሕንፃ ቤተ መቅደስ፤

ንጉሥ ዳዊት በዘመኑ ሕንፃ ቤተ መቅደስ ለማነጽ ቢፈልግም እግዚአብሔር አልፈቀደለትም። ቢሆንም እንዲያንጽ ለተፈቀደለት ለልጁ ለሰሎሞን፦ ወርቁን፥ ብሩን ፥ የከበረውን ድንጋይ ፥ የሚያስፈልገውን ሁሉ አዘጋጅቶ አደራ ሰጥቶታል። ፩ኛዜና ፳፪፥፩-፲፮። ሰሎሞንም እግዚአብሔር ለአባቱ ለዳዊት በተገለጠበት በአሞሪያ ተራራ ዳዊት ባዘጋጀው ስፍራ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ በኢየሩሳሌም የእግዚአብሔርን ቤት ሠራ። ፪ኛ ዜና ፪-፲፯። ቅዳሴ ቤቱም ሲከበር ንጉሡ ሰሎሞን ጸሎቱን በእግዚአብሔር  ፊት አቀረበ። እሳት ከሰማይ ወርዶ የሚቃጠለውን ቁርባን መሥዋዕቱን ሁሉ በላ፤ ይህም የአዲስ ኪዳን መሥዋዕት እሳተ መለኰት የተዋሀደው ለመሆኑ ምሳሌ ነው። የእግዚአብሔርም ክብር ቤተ መቅደሱን ሰለሞላው ካህናቱ በዚያች ዕለት ወደ እግዚአብሔር ቤት መግባት አልቻሉም። የእስራኤልም ልጆች እሳቱንም ክብሩንም ባዩ ጊዜ ድንጋይ በተነጠፈበት ምድር ላይ በግንባራቸው ተደፍተው ሰገዱ። «እርሱ ቸር ነውና፥ ምሕረቱም ለዘላለም ነውና፤» እያሉ እግዚአብሔርን አመሰገኑ። ፪ኛ ዜና ፯፥፩-፫።

          በመጨረሻም እግዚአብሔር ለሰሎሞን በሌሊት ተገልጦ፦ «ጸሎትህን ሰምቻለሁ፤ ይህንም ስፍራ ለራሴ ለመሥዋዕት ቤት መርጫለሁ። --- አሁንም በዚህ ስፍራ ለሚጸለይ ጸሎት ዐይኖቼ ይገለጣሉ፥ ጆሮዎቼም ያደምጣሉ። አሁንም ስሜ ለዘለዓለም በዚያ ይኖር ዘንድ ይህን ቤት መርጫለሁ፥ ቀድሻለሁም። ዐይኖቼና ልቤም ዘወትር በዚያ ይሆናል።» በሎታል። ፪ኛ ዜና ፯፥፲፪-፲፮። ቤተ መቅደሱ በፈረሰ ጊዜም እግዚአብሔር  እንደፈረሰ ይቅር አላለም። «ይህ ሕዝብ የእግዚአብሔር ቤት የሚሠራበት ዘመን አልደረሰም ይላል። በውኑ ይህ ቤት ፈርሶ ሳለ እናንተ ራሳችሁ በተሸለሙ ቤቶቻችሁ ለመኖር ጊዜው ነውን?» በማለት በነቢዩ በሐጌ አድሮ ወቀሳቸው። ያጡትንም ጸጋ ሲነግራቸው፦ «እስኪ በልባቸሁ መንገዳችሁን አስቡ። ብዙ ዘራችሁ፥ ጥቂትም አገባችሁ፤ በላችሁ፥ ነገር ግን አልጠገባችሁም፤ ጠጣችሁ፥ ነገር ግን አልረካችሁም፤ ለበሳችሁ፥ ነገር ግን አልሞቃችሁም፤ ደመወዙን የተቀበለም በቀዳዳ ከረጢት ሰበሰበ።»ብሏቸዋል። ከዚህም አያይዞ፦ “በልባችሁ መንገድ አስቡ ፥ ወደ ተራራው ውጡ ፥ እንጨትንም ቁረ ጡ ፥ ቤትንም ሥሩ ፥ እኔም በእርሱ ደስ ይለኛል ፥ እመሰገናለሁም ።” ሲል አዟቸዋል ። ሐጌ ፩ ፥ ፪-፫ ። በመጨረሻም  “በርቱና ሥሩ ፥ እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ ፤ . . . ከፊተኛው ይልቅ የዚህ የሁለተኛው ቤት ክብር ይበልጣል ፤ . . . በዚህም ስፍራ ሰላምን እሰጣለሁ ፤ . . . ይህን ቤተ መቅደስ ከፍ ለማድረግ ለምትሠራ ሰውነት ሁሉ ሰላምን እሰጣለሁ ።” የሚል ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል ። ሐጌ ፪ ፥ ፩ - ፱

፭፥፫ ፦ የአዲስ ኪዳን ቤተ መቅደስ፤

አዲስ ኪዳንን በደሙ ያጸና ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በምሴተ ሐሙስ ፦ “ስትዩ እምኔሁ ኩልክሙ ፥ ዝ ውእቱ ደምየ ዘሐዲስ ሥርዓት ፥ ዘይትከዓው በእንተ ብዙኃን ለኅድገተ ኃጢአት ። ሁላችሁም ከእርሱ ጠጡ ፤ ኃጢአትን ስለማስተስረይ ፥ ስለብዙዎች የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው ።” ያላችው ለዚህ ነው። ይኸውም የአዲስ ሕግ የወን ጌል ፥ የአዲስ ርስት የመንግሥተ ሰማያት መጽኛ ነው ማለት ነው ። በመሆኑም ሕገ ወንጌል ባለማለፍ ጸንታ የምትኖረው በሥጋውና በደሙ ነው ። የማታልፍ ርስት መንግሥተ ሰማያትም የምትወረሰው በሥጋውና በደሙ ነው ። “የወልደ ዕጓለ እመሕያው ክርስቶስን ሥጋውን ካልበላችሁ ፥ ደሙንም ካልጠጣችሁ ፥ ለእናንተ ሕይወት የላችሁም ብዬ በእውነት እነግራችኋለሁ። ሥጋዬን የበላ ደሜን የጠጣ የማታልፍ መንግሥተ ሰማይን ይወርሳል። ሥጋዬ እውነተኛ መብል ፥ ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና ። ሥጋዬን የበላ ደሜን የጠጣ ከእኔ ጋር ተዋሕዶ ይኖራል፥ እኔም አድሬበት (እሳት ብረትን እንዲዋሀደው በጸጋ ተዋህጄው) እኖራለሁ ።” እንዳለ ። ዮሐ ፮ ፥ ፶፫ -፶፮። ይህም ነፍስ የተለየው መለኮት የተዋሀደው ነው ። የሚሰናዳው ፥ የሚፈተተውና የሚታደለው በአዲስ ኪዳን ቤተ መቅደስ በቤተክርስቲያን ነው ። ከዚህም ጋር እግዚአብሔር ፦ በመዝሙር፥ በቅዳሴ፥ በማኅሌት ይመሰገንበታል ። በአጠቃላይ አነጋገር በሚታይ አገልግሎት የማይታይ ጸጋ የሚታደልባቸው ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን ይፈጸምበታል ። እነዚህም ጥምቀት ፥ ሜሮን ፥ ቁርባን ፥ ክህነት ፥ ተክሊል ፥ ንስሐ ፥ ቀንዲል ናቸው ።

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ በአርባ ቀኑ በሕገ ኦሪት የተጻፈውን ሥርዓት ይፈጽሙለት ዘንድ ወደ ቤተ መቅደስ ወስደውታል ። ሉቃ ፪ ፥ ፳፪ -፳፬ ። ዓሥራ ሁለት ዓመት በሞላው ጊዜም እንደ አስለመዱ ወደ ኢየሩሳሌም ለበዓል ወጡ። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና ጠባቂዋ፥ ዘመዷ፥ አረጋዊ ፥ ጻድቁ ዮሴፍ በየዓመቱ ለፋሲካ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም ይሄዱ ነበር ። በዓሉን ካከበሩ በኋላ ወደ አገራቸው ሲመለሱ ኢየሱስ ክርስቶስ በኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር። ያገኘው ሁሉ በፍቅር ይነጣጠቀው ስለነበር እመቤታችን እና ጠባቂዋ ዮሴፍ የሆነውን አላወቁም። በደረሱም ጊዜ ዕለቱን ፈልገው ስለአላገኙት እየፈለጉት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። በሦስተኛው ቀን በሊቃውንት መካከል ተቀምጦ ሲሰማቸው ሲያሰማቸው፥ ሲጠይቃቸው ሲመልስላቸው አገኙት። ጥያቄውን እና ምላሹን የሰሙት ሁሉ ያደንቁት ነበር።

እናቱ እመቤታችን፦ «ልጄ ለምን እንዲህ አደረግኸን? እኔና አረጋዊው ዮሴፍ ስንፈልግህ ሦስት ቀን ደከምን።» አለችው። «ወይቤሎሙ ለምንት ተሐሥሡኒ እያእመርክሙኑ ከመ ይደልወኒ አሀሉ ውስተ ዘአቡየ ቤት። ለምን ትፈልጉኛላችሁ? በአባቴ ቤት ልኖር እንዲገባኝ አላወቃችሁምን?» አላቸው። በዚህም ቤተመቅደሱን የአባቴ ቤት አለው። ሉቃ ፪፥፵፩-፵፱። በዕለተ ሆሣዕናም ወደ ቤተመቅደስ ገብቶ፦ «ቤቴ የጸሎት ቤት ይሆናል ተብሎ ተጽፏል፤ እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችኋት።» በማለት ሻጮችንና ለዋጮችን አስወጥቷቸዋል። ሉቃ ፲፱፥፵፭=፵፮።

ቅዱሳን ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ዮሐንስ ሰዓት ጠብቀው ወደ ቤተ መቅደስ እየሄዱ ይጸልዩ፥ በዚያም ተአምራት ያደርጉ ነበር የሐዋ ፫፥፩-፲ ይኸውም በየትም ሥፍራ ከሚጸለይ ጸሎት በቤቱ የሚጸለይ ጸሎት ስለሚበልጥ ነው። እግዚአብሔር አንድ ጊዜ፦ «አሁንም በዚህ ስፍራ ለሚጸለይ ጸሎት ዐይኖቼ ይገለጣሉ፥ ጆሮዎቼም ያደምጣሉ።» ብሏልና። ፪ኛ ዜና፥፲፭ ። ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ ቤተ መቅደስ በተመስጦ ይጸልይ የነበረው ለዚህ ነው። ይኸንንም፦ «ወደ ኢየሩሳሌም ከተመለስሁ በኋላ በመቅደስ ስጸልይ ተመስጦ መጣብኝ።» በማለት ገልጦታል። የሐዋ ፳፪፥፲፯። ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ የቤተ መቅደሱ ክብር በሰማይ ስለተገለጠለ ት፦ «በሰማይ ያለው የእግዚአብሔር መቅደስ ተከፈተ፥ የኪዳኑም ታቦት በመቅደሱ ታየ፤» ብሏል። ራእ ፲፩ ፥፲ ፱። በተጨማሪም፦ «ከዚህ በኋላ አየሁ፥ የምስክሩ ድንኳን መቅደስ በሰማይ ተከፈተ።» በማለት ነገሩን አጽንቶታል።

እንግዲህ በብሉይ ኪዳንም በአዲስ ኪዳንም ዘመን የእግዚአብሔር ቤት ቅዱስ መሆኑን ማመን ያስፈልጋል። ንጉሡ ሰሎሞን፦ «የእግዚአብሔር ታቦት የገባችበት ስፍራ ቅዱስ ነው።» ያለው ለዚህ ነውና። ፪ኛ ዜና ፰ -፲፩ ። ከሁሉም በላይ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አካሉን በቤተ መቅደስ መስሏል። ቤተ መቅደሱን ከሻጮችና ከለዋጮች ባጸዳ ጊዜ ደቀመዛሙርቱ፦ «የቤትህ ቅናት በላኝ፤» የሚል ቃል ተጽፎ እንዳለ አሰቡ። መዝ ፷፰፥፱። አይሁድ ግን፦ «ይህን የምታደርግ ምን ምልክት ታሳየለህ?» አሉት። ኢየሱስም፦ «ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፥ በሦስተኛውም ቀን አነሣዋለሁ፤» ብሎ መለሰላችው። አይ ሁድም፦ «ይህ ቤተ መቅደስ በአርባ ስድስት ዓመት ተሠራ፥ አንተስ በሦስት ቀኖች ውስጥ ታነሣዋለህን?» አሉት። እርሱ ግን ይህን የ ተናገረው ቤተ መቅደስ ስለተባለ ሰውነቱ ነበር። ዮሐ ፪፥፲፮-፳፩።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «እኔ ክርስቶስን መስየዋለሁ፤»፩ኛ ቆሮ ፲፩፥፩ እንዳለ፦ ክርስቶስን መስለው የተገኙ ቅዱሳንም አካላቸው በቤተ መቅደስ ተመስሏል። ይኸንንም፦ «የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሆናችሁ፥ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን? ማንም የእግዚአብሔርም ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ።» በማለት ገልጦታል።

፭፥፬፦ ስግደት በቤተ መቅደስ፤

በብሉይም በአዲስም እንደተገለጠው የእግዚአብሔር ቤት ቅዱስ ነው። እንደማንኛውም ቤት ስለአልሆነ ቅዱስ ተብሎ ይቀጸልለታል። በመሆኑም ከሩቅ መሳለም ከቅርብ መስገድ ይገባል። «ወደ ቅዱስ መቅደስህ እሰግዳለሁ፥ ስለ ምሕረትህና ስለ እውነትህም ስምህን አመሰግናለሁ።» እንዲል፤ መዝ ፻፴፪፥፪። «በቅድስናው ስፍራ ለእግዚአብሔር ስገዱ፤» የሚልም አለ። መዝ ፳፰፥፪። በተቀደሰ ስፍራ መስገድ እንዲገባ መንገዱን ያሳየ እግዚአብሔር ነው። በደብረ ሲና ለሙሴ በተገለጠለት ጊዜ፦ «ወደዚህ አትቅረብ፥ አንተ የቆምህባት ስፍራ የተቀደሰች መሬት ናትና፥ ጫማህን ከእግርህ አውጣ።» ብሎታል። በዚህም ለምድሪቱ ቅድስት ብሎ እንደቀጸለላት እናስተውላለን። ዘጸ ፫፥፭። የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም ለኢያሱ ወልደ ነዌ በተገለጠለት ጊዜ፦ «አንተ የቆምህበት ስፍራ የተቀደሰ ነውና ጫማህን ከእግርህ አውልቅ፤» በማለት ነግሮታል። እርሱም መሬቱን ቅዱስ ብሎታል። ቂያ ፭፥፲፭። ሙሴም ኢያሱም በቅድስናው ስፍራ ጫማቸውን አውልቀው ሰግደዋል።

የአዲስ ኪዳን ሐዋርያ ቅዱስ ጴጥሮስም በበኲሉ፦ ጌታ ክብረ መንግሥቱን፥ ግርማ መለኰቱን የገለጠበትን፤ ምሥጢር ሥላሴ በገሀድ የታየበትን፤ ሙሴ ከመቃብር ተነሥቶ ኤልያስ ከሰማይ ወርዶ የጌታን የባህርይ አምላክነት የመሰከሩበትን ተራራ ደብረ ታቦርን «ቅዱስ» ብሎታል። «የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን  ኃይሉንና መምጣቱን ስናስተምራችሁ የተከተልነው የፍልስፍና ተረት አይደለምና፥ የእርሱን ገናንነት እኛ ራሳችን አይተን ነው እንጂ። ከገናናው ክብር፦ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወድደው ልጄ ይህ ነው የሚል ያ ድምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርንና ምስጋናን ገንዘብ አድርጓልና። (ከእርሱ ጋር ትክክል የሆነ ክብሩን፥ ምስጋናውን ፥ የባህርይ አባቱ አብ ልጄ በማለት መስክሮለታልና)። ይህንም ቃል እኛ በተቀደሰው ተራራ (በደብረ ታቦር) አብረነው ሳለን ከሰማይ እንደወረደለት ሰምተነዋል።» በማለት ከነምክንያቱ አብራርቷል። ፪ኛ ጴጥ ፩፥፲፮።

6 comments:

 1. አሜን ቃለህይወት ያሰማልን
  መንግስተ ሰማያት ያውርስልን

  ReplyDelete
 2. አሜን ቃለህይወት ያሰማልን
  መንግስተ ሰማያት ያውርስልን

  ReplyDelete
 3. አሜን ቃለህይወት ያሰማልን
  መንግስተ ሰማያት ያውርስልን

  ReplyDelete