Sunday, October 31, 2010

ነገረ ቅዱሳን/ክፍል ሁለት/

« ቅዱስ » ለፍጡራን ይቀጸላል ?

እግዚአብሔር ከባረካቸውና ከቀደሳቸው ይቀጸልላቸዋል። እርሱ ሰውን ፥ ቦታን ፥ ንዋያትን ቀድሶ የጸጋው መገለጫ ያደርጋቸዋል። በዚህን ጊዜ ከዓለማዊ ግብር ተለይተው ለእግዚአብሔር ብቻ ይሆናሉ።

፫-፩ ቅዱሳን ሰዎች

በዚህ ዓለም በሃይማኖት ጸንተው፥ በምግባር ተገልጠው ፥ በገድል የተቀጠቀጡ ነቢያትና ሐዋርያት፥ ጻድቃንና ሰማዕታት፥ ሊቃውንት፥ካህናትና ምእመናን ቅዱሳን ናቸው። ቅዱስ የሚለው ለፍጡር የማይሰጥ ቢሆን ኖሮ እግዚአብሔር ለእስራኤል ዘሥጋ በሙሴ በኩል፦ «እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ፤» አይላቸውም ነበር። ዘሌ ፲፱፥፪ :: ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም ይኸንን ይዞ፦ «ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁ (ንጽሐ ልቡናን ገንዘብ አድርጋችሁ) ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገ ለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ። አንደሚታዘዙ ልጆች ባለማወቃችሁ አስቀድሞ የኖራችሁበትን ምኞት አትከተሉ። ዳሩ ግን እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደሆነ እናንተ ደግሞ ቅዱሳን ሁኑ።» በማለት እስራኤል ዘነፍስ ለተባሉ ለአዲስ ኪዳን ምእመናን አያስተምራቸውም ነበር። ፩ኛ ጴጥ ፩፥፲፫-፲፮። «ቅዱሳን  ሁኑ፤» የሚለውን የእግዚአብሔርን ቃል አጽንቶ ሲያስተምርም የዓለምን ኅልፈት ከተናገረ በኋላ፦ «ይህ ሁሉ እንዲህ የሚቀልጥ ከሆነ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና እያስቸኮላችሁ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንደምን ልትሆኑ ይገባችኋል»ብሏል። ፪ኛ ጴጥ ፫፥፲-፲፩። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም «በኲራቱም ቅዱስ ከሆነ ቡሆው ደግሞ ቅዱስ ነው፥ ሥሩም ቅዱስ ከሆነ ቅርንጫፎች ደግሞ ቅዱሳን ናቸው፤» ብሏል። ሮሜ ፲፩፥፮፣ ዘኁ~`፲፭፥፳።

ቅዱሳን በሕይወት መጽሐፍ የተጻፉ ናቸው። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ በራእይ መጽሐፉ ስለ ሕይወት መጽሐፍ እግዚአብሔር የተናገረውን ጠቅሷል። ራእ ፳፥፲፪:: ከዚህም ሌላ፦ «ድል የነሣው እንዲሁ በነጭ ልብስ ይጎናጸፋል፥ስሙንም ከሕይ ወት መጽሐፍ አልደመስሰውም፥ በአባቴና በመላእክትም ፊት ለስሙ እመሰክራለታለሁ። መንፈስ ለአብያተክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ፤» የሚል አለ። ራእ ፫፥፭። ነቢዩ ኢሳይያስም፥ «በጽዮን የቀሩ ፥ በኢየሩሳሌምም የተረፉ፥ በኢየሩሳሌም ለሕይወ ት የተጻፉ ሁሉ፥ ቅዱሳን ይባላሉ።» በማለት በመጽሐፈ ትንቢቱ ተናግሮአል። ኢሳ ፬፬። እርሱ እንዲህ አድርጎ ለወንድሞቹ ለቅዱሳ ን ሲመሰክርላቸው፦ የአዲስ ኪዳን ሐዋርያት ደግሞ ለእርሱና ለወንድሞቹ መስክረውላቸዋል። ይኽንንም የሐዋርያት አለቃ ቅዱስ ጴጥሮስ፦ «ይህን በመጀመሪያ ዕወቁ፤ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም። ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፤ ዳሩ ግን ቅዱሳን ሰዎች ከእግዚአብሔር ተልከው በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው ተናገሩ።» በማለት አስተ ምሯል ፪ኛ ጴጥ ፩፥፳። የያዕቆብ ወንድም ይሁዳም፦ ርትዕት ሃይማኖት እንደተሰጠቻቸው፥ በእርሷም እስከሞት ድረስ መጽናታቸውን፥ እኛም እነርሱን አብነት አድርገን መጋደል እንዲገባን፦ «ምሕረትና ሰላም ፍቅርም ይብዛላችሁ ፤ ወዳጆች ሆይ ! ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ ተግቼ ሳለሁ፥ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ስለተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ።» በማለት መልእክቱን አስተላልፏል። ይሁ ፩፥፪-፫። ጻድቁ ካህን ዘካርያስም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ትንቢት ሲናገር ከጥንት ጀምሮ የነበሩትን ነቢያት ቅዱሳን ብሏቸዋል። ሉቃ ፩፥፷፱

፬ አስማተ ቅዱሳን፤

ቅዱሳን ሰዎች የሚጠሩባቸው ስሞች፥ የዓለም ሰዎች እንደሚጠሩባቸው አይደለም። የተቀደስ ነው። ስማቸው ከግብራቸው የተዋሐደ ነው። «ስምን መልኣክ ያወጣዋል፤ » እንደሚባለው ነው። በመሆኑም፦ ዓለማውያን እንደሚሰየሙበት ሥጋዊ፥ ምድራዊ አይደለም። ምናልባት ዓለማውያንም በመንፈሳዊ ስሞች ይጠሩ ይሆናል፥ ነገር ግን ግብራቸው ከስማቸው - ስማቸው ከግብራቸው አይገጥምም። የቅዱሳን ስሞች ግን፦

፬፥፩ እግዚአብሔር ያወጣው ነው፤

አብርሃም የመጀመሪያ ስሙ «አብራም» ነበር፤ አብራም ማለት ታላቅ አባት ማለት ነው። «ከዚህም በኋላ አብራም የዘጠና ዘጠኝ ዓመት ሰው በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር ለአብራም ተገለጠለት፤ እንዲህም አለው፥በፊትህ የሄድሁ ፈጣሪህ እግዚብሔር እኔ ነኝ፤ በፊቴ መልካም አድርግ፥ ንጹሕ ሁን፥ ቃል ኪዳኔንም በአንተና በእኔ መካከል አጸናለሁ፥ እጅግም አበዛሃለሁ። አብራምም በግምባሩ ወደቀ፤ እግዚአብሔርም አብራምን እንዲህ አለው እነሆ ቃል ኪዳኔን በእኔና በአንተ መካከል አጸናለሁ፥ ለብዙ አሕዛብም አባት ትሆናለህ። እንግዲህ ስምህ አብራም አይባልም፥ አብርሃም ይባላል እንጂ፤ ለብዙ አሕዛብ አባት አድርጌሃለሁና።» ይላል ዘፍ ፲፯፥፩-፭

በአዲስ ኪዳንም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ የደቀመዛሙርቱን የቀደመ ስም እየለወጠ አዲስ ስም ሲሰጣቸው ታይቷል። ይኸውም ከተጠሩበትና ከተመረጡበት ሰማያዊ ግብር ጋር የሚገጥም፥የሚዋሐድ ስም ሲሰጣቸው ነው። ቅዱስ ማርቆስ ወንጌላዊ እንደመዘገበው፦ «በየስማቸውም ጠራቸው፤ስምዖንን ጴጥሮስ ብሎ ሰየመው። የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብንና የያዕቆብን ወንድም ዮሐንስንም ቦአኔርጌስ ብሎ ሰየማቸው፤ የነጐድጓድ ልጆች ማለት ነው።» ይላል ማር ፫፥፲፮።

፬፥፪ መልአክ ያወጣው ነው፤

«ወአስተርአዮ መልአከ እግዚአብሔር እንዘ ይቀውም መንገለ የማነ ምሥዋዕ ዘዕጣን። የእግዚአብሔር መልአክ በዕጣን መሠዊያው በስተቀኝ ተገለጠለት፤» የተገለጠው ለዘካርያስ ነው። በቀኝ መገለጡ የማናዊ ነኝ ሲለው ነው፤ አንድም መንገለ የማን (ከግራ ወደ ቀኝ) የምትመለሱበት ዘመን ደርሷል፤ አንድም ከግራ ወደ ቀኝ የሚመልስ ልጅ ትወልዳለህ ሲለው ነው። የቅዱሳን መላእክት ፊታቸው እንደ መብረቅ ስለሆነ ዘካርያስ ፈራ፥ ደነገጠ፥ ተንቀጠቀጠ። ፍርሃት የልቡና ፥ ረዓድ የጉልበት፥ ድንጋጤ የናላ ነው። ከዚያ በፊት በድምፅ ሰምቶት እንጂ በመልክ አይቶት አያውቅም ነበር።

ለመልአክ ፍርሃትን አርቆ መናገር ልማድ ነውና፥ «ኢትፍራህ ዘካርያስ፤ ዘካርያስ ሆይ፥ አትፍራ፤»አለው። ነቢየ እግዚአብሔር ዳንኤልን፦ «ኢትፍራህ ብእሴ ፍትወት ዳንኤል፤» እንዳለው ማለት ነው። ዳን ፲፥፲፪። ፍርሃትን ካራቀለት በኋላም ልክ ለነቢዩ በነገረው መልክ «ጸሎትህ በእግዚአብሔር ፊት ተሰምቷልና፥ ሚስትህ ኤልሳቤጥ ወንድ ልጅንም ትወልድልሃለች፤ ሰሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ። ደስታና ሐሴትም ይሆንልሃል፤ በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል። እርሱ በእግዚአብሔር ፊት ታላቅ ይሆናልና፤» ብሎታል። ሉቃ ፩፥፰ ።

፬፥፫ የተባረከ ነው፤

እግዚአብሔር አብርሃምን፦ «ከአገርህ፥ ከዘመዶችህ፥ ከአባትህም ቤት ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ።» ካለው በኋላ ተስፋውን ነግሮታል። ከተስፋውም መካካል «ስምህንም አከብረዋለሁ፤የሚል ይገኛል። ዘፍ ፲፪፥፪። ይህ ልዑለ ባህርይ እግዚአብሔር የሚያከብረው የሚያሰከብረው ስም በእውነት የተባረከና የተቀደሰ ነው።

፬፥፬ እግዚአብሔር በክብር የጠራው ነው፤

የነቢያት አለቃ ሙሴ የአማቱን የምድያምን ካህን የዮቶርን በጎች ይጠብቅ ነበር። ሙሴ ቅዱስ ጳውሎስ እንደመሰከረለት፦ የንጉሥ የልጅ ልጅ መባልን በእምነት እንቢ ያለ፥ ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን የመረጠ፥ የክርስቶስ የመስቀሉ ተግዳሮት ከግብፅ ሀብት ሁሉ ይልቅ እጅግ የሚበልጥ ባለጠግነት አንደሚሆን ያወቀ፥ዋጋውን አሻግሮ የተመለከተ፥ የንጉሡን ቁጣ ሳይፈራ የግብፅን ሀገር በእምነት የተወ፥ ከሚያየው ይልቅ የማይታየውን ሊፈራ የወደደ ሰው ነው። ዕብ ፲፩፥

ሙሴ በጎቹን ወደ ምድረ በዳ ነዳ፥ ወደ እግዚአብሔርም ተራራ ወደ ኮሬብ ወጣ። እግዚአብሔርም የደብረ ሲናን ሐመልማል ተዋህዶ በእሳት ነበልባል አምሳል ተገለጠለት። ሐመልማል የእመቤታችን፥ ነደ እሳት የመለኰት ምሳሌዎች ናቸው። ሙሴ ነበልባልና ሐመልማል ሳይጠፋፉ ተዋህደው ባየ ጊዜ ተደነቀ። «ቊጥቋጦው ስለምን አልተቃጠለም?ልሂድና ይህን ታላቅ ራእይ ልይ፤» አለ። እግዚአብሔርም እርሱ ይመለከት ዘንድ እንደመጣ ባየ ጊዜ፦ «ሙሴ፥ ሙሴ ሆይ፥» ብሎ ጠራው ዘጸ ፫፥፩-፬። «ሆይ» የሚለው ቃል ቃለ አክብሮ ነው። ለፍፃሜው ሐመልማለ ሲና በምትባል በእመቤታችን አድሮ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ በመወለድ ሐዋርያትን፣ ሰብዓ አርድዕትን እና ቅዱሳት አንስትን ለሰማያዊ ግብር እንደሚጠራቸው ያመለክታል።

እግዚአብሔር ነቢዩ ሳሙኤልንም በክብር ጠርቶታል። የስእለት ልጅ ነበር፤ ጡት ከጣለበት ጊዜ ጀምሮ ያደገው በእግዚአብሔር  ቤት በእግዚአብሔር ፊት ነው። ያ ዘመን የእግዚአብሔር ድምፅ ከአገልጋዮችም ከተገልጋዮችም የራቀበት ዘመን ነበር፤ ሳሙኤል ግን ገና ብላቴና ሳለ የበፍታ ኤፉድ ታጥቆ በእግዚአብሔር ፊት ያገለግል ነበር። እናቱም ትንሽ መደረቢያ ሠራችለት፤ በየዓመቱም መሥዋዕት ለመሠዋት ከባልዋ ጋር ስትወጣ ትወስድለት ነበር። ሊቀ ካህናቱ ዔሊም መክነው ያገኙትን ልጃቸውን በእምነት ለእግዚአብሔር በመስጠታቸው «በምትክ ዘር ይስጣችሁ፤» ብሎ ባረካቸው። እግዚአብሔርም በምትኩ ሦስት ወንዶች እና ሁለት ሴቶችን ሰጣቸው። ብላቴናው ሳሙኤልም በእግዚአብሔር ፊት አደገ ፪ኛ ሳሙ ፪፥፲፭-፳፮።

የእግዚአብሔር መብራት ገና ሳይጠፋ ሳሙኤል የእግዚአብሔር ታቦት ባለበት በእግዚአብሔር መቅደስ ተኝቶ ነበር። በዚህን ጊዜ ነው፥ እግዚአብሔር በታቦቱ አድሮ «ሳሙኤል፥ ሳሙኤል ሆይ፥» እያለ በአንድ ሌሊት አራት ጊዜ መላልሶ የጠራው። እርሱ ግን እግዚአብሔርን ገና በድምፅ ስላላወቀው ፥ ሊቀ ካህናቱ ዔሊ የጠራው መስሎት፦ «እነሆ፥ የጠራኸኝ፤» እያለ ተመላልሶ ነበር። ዔሊም እግዚአብሔር ብላቴናውን በክብር እንደጠራው አስተውሎ፦ «ልጄ፥ ሄደህ ተኛ፤ ቢጠራህም፦ አቤቱ ባሪያህ ይሰማል ተናገር በለው።» ሲል መከረው። ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር በእስራኤል ሊያደርገው ያሰበውን ምሥጢር ሁሉ ለብላቴናው ነግሮታል። ሳሙኤልም እሰኪነጋ ተኛ፥ማልዶም ተነሥቶ የእግዚአብሔርን ቤት ደጅ ከፈተ። ራእዩንም ለዔሊ መንገር ፈራ። ዔሊ ግን «ልጄ ሳሙኤል ሆይ፥» በማለት ስሙን በክብር ከጠራ በኋላ «እግዚአብሔር የነገረህ ነገር ምንድን ነው? ከእኔ አትሸሽግ፤» አለው። በእግዚአብሔርም ስም አማጸነው። ሳሙኤልም አንዳችም ሳይሸሽግ ነገሩን ሁሉ ነገረው። በዚህን ጊዜ ዔሊ «እርሱ እግዚአብሔር ነው፥የወደደውን ደስ ያሰኘውን ያድርግ፤» አለ። ፩ኛ ሳሙ ፫፥፩-፲፰።

ነቢዩ ኤርምያስም፦ «ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል፦ ኤርምያስ ሆይ! ምን ታያለህ? እያለ ወደ እኔ መጣ። እኔም የሎሚ በትር እያለሁ፥ አልሁ። እግዚአብሔርም፥ የተናገርሁትን እፈጽመው ዘንድ እተጋለሁና መልካም አይተሃል አለኝ፤» ብሏል። የሎሚ በትር የተባለች እመቤታችን ናት። ሎሚ መዓዛ አለው ፥ ይህም ለመዓዛ ድንግልናዋ ምሳሌ ነው። ኤር ፩፥፲፩። እግዚአብሔር ነቢዩ ሕዝቅኤልንም ለነቢይነት በጠራው ጊዜ፦ «የሰው ልጅ ሆይ! በእግርህ ቁም እኔም እናገራለሁ፤ --- የስው ልጅ ሆይ እኔን ወደ አስመረሩኝ ወደ እስራኤል ቤት እልክሃለሁ። እነርሱና አባቶቻቸው እስከ ዛሬ ዐመፁብኝ። እነርሱ ፊታቸው የከፋ፥ ልባቸው የደነደነ ልጆች ናቸው። እኔ ወደ እነርሱ እልክሃለሁ፤ አንተም፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል በላቸው። --- አንተ የሰው ልጅ ሆይ! ኲርንችትና እሾህ ከአንተ ጋር ቢኖሩም፥ አንተም በጊንጦች መካከል ብትቀመጥ፥ አትፍራቸው፤ ቃላቸውንም አትፍራ፤--- ከፊታቸውም የተነሣ አትደንግጥ፤ እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ናቸውና። --- አንተ የሰው ልጅ ሆይ! የምነግርህን ሰማ፤ ---- አፍህን ክፈት፥ የምሰጥህንም ብላ። ---- የሰው ልጅ ሆይ! ያገኘኸውን ብላ፤ ይህን መጽሐፍ ብላ፤ ሄደህም ለእስራኤል ልጆች ተናገር። ---- የሰው ልጅ ሆይ! አፍህ ይብላ፥ በምሰጥህም በዚህ መጽሐፍ ሆድህን ሙላ። --- የሰው ልጅ ሆይ!ተነሥተህ ወደ እስራኤል ቤት ሂድና ግባ፥ ቃሌንም ንገራቸው።» ብሎታል። ሕዝ ፪፥፩-፲ ፤ ፫፥፩-፬፤ እርሱም፦ «እኔም በላሁት፥ በአፌም ውስጥ እንደ ማር ጣፈጠ፤» ብሏል። እግዚአብሔር ነቢዩ ሕዝቅኤልን እስከ መጨረሻው ድረስ ያነጋገረው «የሰው ልጅ ሆይ! » እያለ ነው። ይኸውም በመጨረሻው ዘመን (ዓመተ ዓለም፥ ዓመተ ፍዳ፥ ዓመተ ኲነኔ ሲፈጸም) በተዋህዶ ሰው ሆኖ እንደሚወለድ ሲገልጥለት ነው።
         
፬፥፭፦ ቅዱሳን መላእክት በክብር የጠሩት ነው፤

ነቢዩ ዳንኤል አይቶት የነበረው ድንቅ ራእይ ይገለጥለት ዘንድ፥ ስለ ራሱም፥ ስለ ወገኖቹም ሱባኤ ገብቶ ነበር። ምክንያቱም ከራእዩ የተነሣ አያሌ ቀን ታምሞ ነበርና ነው። ማቅ ለብሶ አመድ ላይ ተኛ። ይጸልይና ይለምን (ይማልድ) ዘንድ ፊቱን ወደ ጌታ ወደ አምላክ አቀና። በትህትና ራሱን ከዓመፀኞች ጋር ቆጥሮ፦ «ጌታ ሆይ! ከሚወዱህና ትእዛዝህን ከሚፈጽሙ ጋር ቃል ኪዳንን እና ምሕረትን የምትጠብቅ ታላቅና የምታስፍራ አምላክ ሆይ! ኃጢአትን ሠርተናል፥ በድለንማል፥ ክፋትንም አድርገናል፥ ዐምፀንማል፥ ከትእዛዝህና ከፍርድህም ፈቀቅ ብለናል።» አለ። «ጌታ ሆይ! በፍጹም ቸርነትህ ቁጣህንና መቅሠፍትህን ከከተማህ ከኢየሩሳሌምና ከተቀደሰው ተራራህ መልስ፤ ስለ ኃጠአታችንና ስለ አባቶቻችን  በደል ኢየሩሳሌምና ሕዝብህ በዙሪያችን ላሉት ሁሉ (በአሕዛብ ዘንድ) መሰደቢያ ሆነዋልና።» እያለ ተማጸነ። «አምላኬ ሆይ! በፊትህ የምንለምን ሰለ ብዙ ምሕረትህ ነው እንጂ ስለ ጽድቃችን አይደለምና፥ ጆሮህን አዘንብለህ ስማ፤ ዐይንህንም ገልጠህ ጥፋታችንን እና ስምህ የተጠራበትን ከተማ ተመልከት። አቤቱ ስማ፥ አቤቱ ይቅር በል፥ አቤቱ አድምጥና አድርግ፤ አምላኬ ሆይ! ስምህ በከተማህና በሕዝብህ ላይ ተጠርቷልና ስለ ራስህ አትዘ ግ ይ ።» እያለ ማለደ። በዚህ ዓይነት ኹኔታ ሲጸልይ፥ ሲማልድ አስቀድሞ በጸሎቱ መጀመሪያ አይቶት የነበረው ገብርኤል እየበረረ ወ ደ  እርሱ መጣ። በማታም መሥዋዕት ጊዜ ዳሰሰው፤አስተማረው፥ ተናገረውም፤ «ዳንኤል ሆይ! ጥበብና ማስተዋልን እሰጥህ ዘንድ አ ሁን መጥቻለሁ። አንተ እጅግ የተወደድህ ሰው ነህና በልመናህ መጀመሪያ ላይ ቃል ወጥቷል፥ እኔም እነግርህ ዘንድ መጥቻለሁ፤ አሁንም ነገሩን መርምር፥ ራእዩንም አስተውል፤» አለው። ዳን ፰፥፲፭-፳፯።

ነቢዩ ዳንኤል በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ በሦስተኛው ዓመተ መንግሥትም ራእይ ተገልጦለት ነበር። በራእዩ ውስጥም ታላቅ ኃይልና ማስተዋልም ተሰጥቶት ነበር። በዚህም ጊዜ ማለፊያ እንጀራ ሥጋም ሳይበላ፥ የወይን ጠጅም ሳይጠጣ፥ ዘይትም ሳይቀባ ሦስት ሳምንት ሙሉ አዘነ፥ ጾመ። አካሉ እንደ ቢረሌ፥ ፊቱም እንደ መብረቅ፥ ዐይኖቹም እንደሚንበለበል ፋና፥ ክንዶቹና እግሮቹም እንደ ጋለ ናስ፥ የቃሉም ድምፅ እንደ ብዙ ድምፅ የሆነ በራእይ ተገለጠለት። ብቻውን ስለጾመ ብቻውን ራእዩን አየ። በአፍ ጢሙም ፍግም ብሎ ተደፋ፥ በጉልበቱ ተንበረከከ፥ ሰገደ። እነሆ እጅ ዳሰሰው፥ እጁንም ይዞ በጉልበቱ አቆመው። «እጅግ የተወደድህ ሰው ዳንኤል ሆይ! እኔ ዛሬ ወደ አንተ ተልኬአለሁና የምነግርህን ቃል አስተውል፥ ቀጥ ብለህም ቁም።» አለው። እየተንቀጠቀጠም ቆመ። ደግሞም «ዳንኤል ሆይ!አትፍራ፤ ልብህ ያስተውል ዘንድ፥ ሰውነትህም በአምላክህ ፊት ይዋረድ ዘንድ ከአደረግህበት ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ቃልህ ተሰምቷል፤ እኔም ስለ ቃልህ መጥቻለሁ፤» አለው። አሁንም ፊቱን ወደ ምድር ደፍቶ ሰገደ፥ ዲዳም ሆነ። እነሆም የሰው ልጅ የሚመስል ከንፈሩን ዳሰሰው፥ ያን ጊዜም አፉን ከፍቶ ተናገረ፥ በፊቱ ቆሞ የነበረውንም፦ «ጌታ ሆይ! ከራእዩ የተነሣ ሰ ውነቴ ታወከች ፥ ኃይልም አጣሁ። አቤቱ አገልጋይህ ከጌታዬ ጋር ይናገር ዘንድ አንዴት ይችላል? ከአሁንም ጀምሮ ኃይሌ አይጸናም፤ እስትንፋስም አልቀረልኝም፤» አለው። የስው ልጅ የሚመስለውም ዳሰሰውና አበረታው። ሦስተኛም፦ «እጅግ የተወደድህ ሰው ሆይ! አትፍራ ሰላም ለአንተ ይሁን፥ በርታ፥ ጽና፤» አለው። እርሱም በረታ። ዳን ፲፥፩-፲፱

፬፥፮፦ ነገረ እግዚአብሔርን የሚናገር ነው

የቅዱሳን ስማቸው የእግዚአብሔርን ማንነት የሚገልጥና የሚያስተምር ነው። ሳሙ-ኤል ማለት የእግዚአብሔር ስም ማለት ነው። ኤልያስ ማለት ኃይለ እግዚአብሔር ማለት ነው። ኢሳይያስ ማለት እግዚአብሔር መድኃኒት ማለት ነው። ኢዩኤል ማለት እግዚአብሔር አምላክ ማለት ነው። ኢያሱ ማለት እግዚአብሔር አዳኝ ማለት ነው። ኤልሳዕ ማለት እግዚአብሔር ደኅንነት ማለት ነው። ኤርምያስ ማለት እግዚአብሔር ከፍ ያደርጋል ማለት ነው። ሚክያስ ማለት እግዚአብሔርን የሚመስል ማነው? ማለት ነው። ዳንኤል ማለት እግዚአብሔር ዳኛ ማለት ነው። ዘካርያስ ማለት እግዚአብሔር ያስተውላል ማለት ነው። አዛርያ ማለት እግዚአብሔር ይረዳዋል ማለት ነው። ሚሳኤል ማለት እግዚአብሔርን የሚመስል ማለት ነው። ሶፎንያስ ማለት እግዚአብሔር ሰውሮአል ማለት ነው። አብድዩ ማለት የእግዚአብሔር አገልጋይ ማለት ነው። ሕዝቅኤል ማለት እግዚአብሔር ብርታትን ይሰጣል ማለት ነው። ዮሐንስ ማለት የእግዚአብሔር ጸጋ ማለት ነው። ናትናኤል ማለት የእግዚአብሔር ስጦታ ማለት ነው። ቤተክርስቲያን የልጅነትን ጥምቀት በምታጠምቅበት ጊዜ ስመ ክርስትና የምትሰጠው ለዚህ ነው።

፬፥፯ መማጸኛ ነው።

እግዚአብሔር ከሚለመንባቸው መንገዶች አንዱ በቅዱሳን ስም የሚቀርብ ተማኅጽኖ ነው። የወዳጆቹን ስም እየጠራን ስንማጸነው ይለመነናል። እርሱ ራሱ ያከበረው የቀደሰው ስም ነውና። በመሆኑም ስማቸው ብቻ ስለተጠራ በረከት አለ። ክፉ የሚባል ሰው እንኳ በሚወደው በአባቱ፥ በእናቱ፥ በልጁ ስም ሲማጸኑት ይለመናል። ሞተውም ከሆነ «በአባትህ አጥንት፥ በእናትህ አጥንት፥ በልጅህ አጥንት» ይሉታል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ኃጢአተኞችና በደለኞች ብቻ ሳይሆኑ ቅዱሳንም በቅዱሳን ስም ሲማጸኑ፥ የቅዱሳንን ስም መማጸኛ ሲያደርጉ ታይተዋል። ነቢዩ ኤልያስ ለእግዚአብሔር ቀንቶ በጸሎት ሦስት ዓመት ከመንፈቅ ዝናብ ለዘር ጠል ለመከር ከከለከለ በኋላ፦ እግዚአብሔር «ሂድና ለንጉሡ ለአክዓብ ተገለጥለት፤» አለው። በሰማርያ ራብ ጸንቶ ነበር። አከዓብም ኤልያስን ባየው ጊዜ «እስራኤልን የምትገለባብጥ (ከባሕር እንደወጣ ዓሣ በውኃ ጥም የምታገላብጠው፥ ወፍራሙን ቀጭን፥ ቀዩን ጥቁር፥ ጥቁሩን ነጭ የምታደርገው አንተ ነህን?» አለው። ኤልያስም «እግዚአብሔርን ትታችሁ በዓሊምን የተከተላችሁ፥ አንተና የአባትህ ቤት ናችሁ እን ጂ እኔስ እስራኤልን አልገለባብጥም። አሁንም ወደ እስራኤል ሁሉ ልከህ አራት መቶ ሃምሣ ነቢያተ ሐሰትን፥ አራት መቶ የማምለኪያ ዐፀድ ነቢያትን ወደ እኔ ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ሰብስብ፤ » አለው። የንጉሥ ትእዛዝ ነውና እነርሱም ሕዝቡም ተሰበሰ ቡ።

ነቢዩ ኤልያስ ወደ ሕዝቡ ቀርቦ፦ «እስከ መቼ በሁለት ልብ ታነክሳላችሁ? እግዚአብሔር አምላክ ቢሆን እርሱን ተከተሉ፥ በዓልም አምላክ ቢሆን እርሱን ተከተሉ፤» ብሎ ወቀሳቸው። አንዲት ቃል እንኳ አልመለሱለትም። ቀጥሎም፦ «ከእግዚአብሔር ነቢ ያት አንድ እኔ ብቻ ቀርቻለሁ፤ እነርሱ ግን ስምንት መቶ ሃምሣ ናቸው። ሁለት ወይፈኖች ይስጡንና መሥዋዕት እንሠዋ፤ እነርሱም የአምላካቸውን ስም ይጥሩ፥ እኔም የፈጣሪዬን የእግዚአብሔርን ስም እጠራለሁ፤ ሰምቶም በእሳት የሚመልስ እርሱ አምላክ ይሁን፤» አላቸው። ሕዝቡም «ይህ ነገር መልካም ነው፤» አሉ።

ኤልያስ የበዓልን ነቢያት፦«እናንተ ብዙዎች ናችሁና አስቀድማችሁ አንድ ወይፈን ምረጡና አዘጋጁ፥ የአምላካችሁንም ስም ጥሩ፥ በበታቹም እሳት አትጨምሩ፤» አላቸው። መሥዋዕታቸውን አዘጋጅተው «በዓል ሆይ፥ ስማን፤» እያሉ ቢጮኹ፥ መሠዊያውን እየዞሩ ቢያነክሱ ሰሚ ጠፋ። ለወትሮው ቀረብ በሎ «አቤት» የሚላቸው ሰይጣን የእግዚአብሔር ሰው ኤልያስ ስላለ መቅረብም ድ ምፅ ማሰማትም አልቻለም። የራሱን ሳይሆን የእግዚአብሔርን ክብር የሚፈልግ ኤልያስም፦ «አምላክ ነውና በታላቅ ቃል ጩኹ፥ ምናልባት ጨዋታ ይዞ ወይም አሳብ ይዞት ወይም ተኝቶ እንደሆነ መቀስቀስ ያስፈልገዋል።» እያለ ይዘብትባቸው ጀመር። በታላቅ ቃል እየጮኹ፥ እንደልማዳቸው ደማቸው እስኪፈስ ድረስ ገላቸውን ቢቧጭሩ፥ እስከ ሠርክ ድረስ ትንቢት ቢናገሩ፥ የሚመልስና የሚያዳምጥ አልነበረም።

ነቢዩ ኤልያስ እነርሱን፦ «እንግዲህስ ወዲያ በቃችሁ ወግዱ፥ሂዱም፤ እኔም መሥዋዕቴን እሠዋለሁ።» ካላቸው በኋላ፦ በአሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል ልክ አሥራ ሁለት ድንጋይ ወስዶ መሠዊያ ሠራ። የፈረሰውንም መሠዊያ አደሰ። በመሠዊያው ዙሪያ ሁለት መስፈሪያ እህል የሚይዝ ጉድጓድ ቈፈረ። በመሠዊያው ላይ እንጨት ደረደረ። ወይፈኑንም በብልት በብልት ቆርጦ በእንጨቱ ላይ አኖረ። ጉድጓዱ ሞልቶ ውኃው በመሠዊያው ዙሪያ እስኪፈስስ ድረስ አሥራ ሁለት ጋን ውኃ አስፈሰሰበት። በመጨረሻም፦ «አቤቱ የአብርሃምና የይስሐቅ የያዕቆብም አምላክ ሆይ! ስማኝ፤ ዛሬ በእሳት ስማኝ፤» ብሎ በቅዱሳን አባቶቹ ስም ተማጸነ። እሳትም ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወረደች፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ እንጨቱንም፥ ድንጋዩንም በላች፤ (አቃጠለች)፤በጉድጓዱም ውስጥ ያለውን ውኃ አፈሩንም ላሰች። ሕዝቡም በግምባራቸው ተደፍተው፦ «እግዚአብሔር በእውነት እርሱ አምላክ ነው፥ እግዚአብሔር እርሱ አምላክ ነው፤» አሉ። ፩ኛ ነገ ፲፰፥፩-፵።

እስራኤል ዘሥጋ በግብፅ ሳሉ ከባርነት የተነሣ አልቅሰው ጮኸው ነበር፤ ስለ ባርነታቸውም ጩኸታቸው ወደ እግዚአብሔር ወጣ። እግዚአብሔርም ጩኸታቸውን ሰማ። የጮኹት በአባቶቻቸው በአብርሃም በይስሐቅ በያዕቆብ ስም ነው። እግዚአብሔርም ከአብርሃምና ከይሰሐቅ ከያዕቆብም ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን አስቦ ጐበኛቸው ታወቀላቸውም። ዘጸ ፪፥፳፫-፳፭።

ነቢዩ ኤልያስ በእሳት ፈረሶች በሚሳብ በእሳት ሰረገላ ወደ ሰማይ በሚያርግበት ጊዜ መጠምጠሚያውን ለኤልሳዕ ጣለለት። በኤልሳዕም ራስ ላይ ዐረፈ። ኤልሳዕም ተመልሶ በዮርዳኖስ ዳር ቆመ። በራሱ ላይ ያረፈችውን የኤልያስን መጠምጠሚያ ወስዶ ወኃውን መታባት፦ ውኃው ግን አልተከፈለም። ያልተከፈለው ዝም ብሎ በመምታቱ ነው። በኋላ ግን «የኤልያስ አምላክ እግዚአብሔር ወዴት ነው? እንዴትስ ነው?» እያለ በመምህሩ ስም እየተማጸነ ቢመታው ዮርዳኖስ ለሁለት ተከፍሎለታል። ፪ኛ ነገ ፪፥፩-፲፬።

4 comments:

 1. ቃለ ህይወት ያሰማልን መልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ:: ከእርሶ ብሎግ ብዙ እንድማር እጠብቃለሁ:
  እግዚእብሄር ጸጋውን ያብዛሎት ያገልግሎት ዘመኖን ያርዝምልን::

  ReplyDelete
 2. kale hiwot yasemalen abatachen, sle kirstena sim sinesa tiz alegn, sahile mariam new kirstena sime blew welajoche negrewignal, min malet endehone tirgumun yenegrugnal? leand and abatoch senegrachew gir yelachewal. lehuletum tsota yehonal weyes endet new? egziabher yestelegn.

  ReplyDelete
 3. ቃለ ህይወት ያሰማልን መልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ:: ከእርሶ ብሎግ ብዙ እንድማር እጠብቃለሁ:
  እግዚእብሄር ጸጋውን ያብዛሎት ያገልግሎት ዘመኖን ያርዝምልን

  ReplyDelete
 4. May God bless you

  ReplyDelete