Sunday, October 31, 2010

ነገረ ማርያም ክፍል ፪

፩ « ታላቅ ምልክት በሰማይ ታየ ፤ » ራእ ፲፪ ፥ ፩ - ፪ ።

          እግዚአብሔር ፦ በምሳሌ ፥ በትንቢት ፥ በሕልም ፥ በራእይና በገሃድ በወዳጆቹ በኲል መልእክቱን ያስተላልፋል። ኃላፊያቱንና መጻእያቱን ይናገራል። ኃላፊውን በመጻኢ ፥ መጻኢውን በኃላፊ አንቀጽ የሚናገርበት ጊዜም አለ። በመሆኑም ፦ ንባቡን የሚተረጉም ፥ ትርጓሜውን የሚያመሰጥር ፥ ምስጢሩን አምልቶ አስፍቶ የሚፈትት ( የሚተነትን ) ያስፈልጋል።
-       « እከስት በምሳሌ አፉየ ፥ ወእነግር አምሳለ ዘእምትካት ፤ አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ ፥ ( ነገሬን በምሳሌ እገልጣለሁ ፥ ወንጌልን በምሳሌ አስተምራለሁ ) ፥ ከቀድሞ ጀምሮ ያለውንም ምሳሌ እናገራለሁ፤ » ምሳ ፸፯ ፥ ፪ ፣ ማቴ ፲፫ ፥ ፴፭።
-       « ወይቤሎሙ ፥ ስምዑ ቃልየ ፥ ለእመቦ ዘኮነ ነቢየ እምኔክሙ ለእግዚአብሔር በራእይ አስተርኢ ሎቱ ፥ ወበሕልም እትናገሮ። ነገሬን ስሙ ፥ ከእናንተ ለእግዚአብሔር ነቢይ የሆነ ሰው ቢኖር በራእይ እገለጽለታለሁ ፥ በሕልም እነጋገረዋለሁ አላቸው። » ዘኁ ፲፪ ፥ ፮
-       « ወአኮ ከመ ቊልዔየ ሙሴ ፥ ምእመን ውእቱ ላዕለ ኲሉ ቤትየ ፤ አፈ በአፍ እትናገሮ ገሃደ ወአኮ በስውር ፥ ወርእየ ስብሐተ እግዚአብሔር። ነገር ግን የምናገረው እንደታመነ ወዳጄ እንደ ሙሴ አይደለም ፥ እሱ በወገኖቼ በእስራኤል ሁሉ የታመነ ነውና ፤ ተገልጬ ቃል በቃል እነጋገረዋለሁ እንጂ
በራሕይ በሕልም የምነጋገረው አይደለም ፥ የእግዚአብሔርነቴን ጌትነትም ያየ እሱ ነው። » ዘኁ ፲፪ ፥ ፯
- « ይህን መጀመሪያ ዕወቁ ፥ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም። ትንቢተ ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና ፤ ዳሩ ግን ቅዱሳን ሰዎች ከእግዚአብሔር ተልከው በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው ተና ገሩ ።» ፩ኛ ጴጥ ፩ ፥፳
          ቅዱስ ዮሐንስ በፍጥሞ ደሴት ተግዞ ሳለ የተገለጠለትን ራእይ ሲናገር። « ወአስተርአየ ተአምር ዐቢይ በውስተ ሰማይ ፤ ታላቅ (ደገኛ የሆነ) ምልክት በሰማይ ታየ ፤ » ብሏል። ቅዱስ ዮሐንስ ይህን ምልክት ፦  ታላቅ ፥ ገናና ፥ ብርቱ ፥ ፍጹም ፥ በማለት የተናገረው ከእግዚአብሔር በመሆኑ ነው። እግዚአብሔር ታላቅ ነውና። ይኽንንም ቅዱስ ዳዊት ፦ « ዐቢየ እግዚአብሔር ፥ ወዐቢየ ኃይሉ ፤ እግዚአብሔር ታላቅ ነው  ፥ ( እግዚአብሔር አብ ገናና ነው ) ፥ ኃይሉም ታላቅ ነው ፤ ( ኃይሉ እግዚአብሔር ወልድም ገናና ነው ) ፤ ወአልቦ ኁልቊ ለጥበቡ ። ለጥበቡም ቁጥር የለውም ። ( ጥበቡ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም ሀብቱ ፍጹም ነው )። » በማለት ተናግሮታል። መዝ ፩፻፵፮ ፥ ፭ ። እግዚአብሔር ታላቅ በመሆኑ ተአምራቱም ታላላቅ ናቸው። « እግዚአብሔርን አመስግኑት ቸር ነውና ፥ . . . የአማልክትን አምላክ አመስግኑ ፤ . . . . . የጌቶችን ጌታ አመስግኑ ፤ . . . . . . እርሱ ብቻውን ታላላቅ ተአምራትን ያደረገ ፥ ምሕረቱ ለዘለላም ነውና ፤ » ይላል። መዝ ፩፻፴፭ ፥ ፩-፬ ።
          ይህ ምልክት በሰማይ መታየቱ ምድራዊ ያይደለ ሰማያዊ ፥ ሥጋዊ ያይደለ መንፈሳዊ ክብርን ፥ ልዕልናን ያሳያል። ይህ ምልክት የታየበት ሰማይ የሚያልፈው ፥ የሚጠፋው ሰማይ አይደለም። ዛሬ የምናያቸው ሰማይና ምድር ያልፋሉ። ማቴ ፭ ፥ ፲፰ ፣ ምልክቱ የታየው ጸ ንተው  በሚኖሩት ሰማያት ነው። ምክንያቱም ራሱ ቅዱስ ዮሐንስ ፦ « አዲስ ሰማይና አዲስ ምድርን አየሁ ፤ የፊተኛው ሰማይና የፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና ፤ » ብሏል። ራእ ፳፩ ፥ ፩። ቅዱስ ጴጥሮስም ፦ ሰማይና ምድር እንደሚያልፉ ፥ እንደሚጠፉም ከተናገረ በኋላ፦ « እኛ ግን ጽድቅ የሚኖርባቸውን አዲሶቹን ሰማያትና አዲሲቱን ምድር ተስፋ እናደርጋለን ። » ብሏል። ፩ኛ ጴጥ ፫ ፥ ፲ -፲፫ ።
፪፦ « ፀሐይን የተጐናጸፈች ፤ »
          ፀሐይ ቀንን እንዲገዛ የተፈጠረ ነው።  « ለፀሐይ ቀንን ያስገዛው ምሕረቱ ለዘላለም ነውና ፤ » ይላል። መዝ ፩፻፴፭ ፥ ፰። የፀሐይ ተፈጥሮ ከእሳት ስለሆነ ትሞቃለች ፥ ትደምቃለች። ብርሃኗም ከጨረቃ ብርሃን ሰባት እጥፍ ነው። ሄኖ ፳፩ ፥ ፶፮ ። እግዚአብሔር ማክሰኞ ማታ ለረቡዕ አጥቢያ ፦ « ለይኩን ብርሃን ውስተ ጠፈረ ሰማይ ፤ ብርሃን በሰማይ ጠፈር ይሁን ፤» ባለ ጊዜ ጸሐይ ጨረቃ ከዋክብት ተፈጥረዋል። ዘፍ ፮ ፥ ፲፮ ። በዚህን ጊዜ መላእክት በታላቅ ድምጽ አመስግነውታል። « ወአመ ተፈጥሩ ከዋክብት ሰብሑኒ ኲሎሙ መላእክትየ በዓቢይ ቃል ፤ ከዋክብት በተፈጠሩ ጊዜ መላእክቴ ሁሉ በታላቅ ድምጽ አመሰገኑኝ ፤» እንዳለ ። ኢዮ ፴፰ ፥ ፯ ።
          የተፈጠሩበት ዓላማም በዚህ ዓለም እንዲያበሩ ፥ (ጨለማን እንዲያርቁ) ፥ በመዓልትና በሌሊት መካከል ድንበር ሆነው እንዲለዩ ፥ ማለትም መለያ ምልክት እንዲሆኑ ፥ አንድም ለሰው ልጅ ምሳሌ እንዲሆኑ ነው። ፀሐይ መውጣቷ የመወለዳችን ፥ በጠፈር ላይ ማብራቷ በዚህ ዓለም የመኖራችን ፥ መግባቷ ( በምዕራብ መጥለቋ ) የመሞታችን ፥ ተመልሳ በምሥራቅ መውጣቷ የመነሣታችን ምሳሌ ነው። ከዚህም ሌላ ፦ ክረምት ፥ በጋ ፥ ጸደይ ፥ መጸው ብሎ አራት ክፍለ ዘመን ለመቊጠር ፥ ለሳምንት ሰባት ቀን ብሎ ለመቊጠር ፥ ሦስት መቶ ስድሳ አምስቱን ቀን ዓመት ብሎ ለመቊጠር ምልክት ይሆኑ ዘንድ ፀሐይን ጨረቃን ከዋክብትን ፈጠረ።
፪ ፥ ፩፦ ኢየሱስ ክርስቶስ ፀሐይ ነው ፤
          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፀሐይ ተመስሏል። « ወይሠርቅ ለክሙ ለእለ ትፈርሁ ስምየ ፀሐየ ጽድቅ ፤ ነገር ግን ስሜን ለምትፈሩት ለእናንተ የጽድቅ ፀሐይ ይወጣላችኋል ፤ ( ፀሐየ ጽድቅ ክርስቶስ ይወለድላችኋል ) ፤ ይላል። ሚል ፬ ፥ ፪። ይኸውም ይታወቅ ዘንድ በቅዱሱ ተራራ በደብረ ታቦር በነቢያትና በሐዋርያት ፊት ገጹ እንደ ፀሐይ በርቷል። « ወአብርሃ ገጹ ከመ ፀሐይ ፤ ፊቱ እንደ ፀሐይ ብሩህ ሆነ ፤ ( ጌትነቱን ገለጸ ) ፤ » ይላል። ማቴ ፲፯ ፥ ፪ ።
          ፀሐይ በጠፈረ ሰማይ ሆና እንደምታበራ ፥ በሰማይ የሚኖር እርሱ ብርሃናችን ነው። « እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ ፥ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃንን ያገኛል እንጂ በጨለማ ውስጥ አይመላለስም። ( ወደ ከህደት አይሄድም )። ብሏልና ። ዮሐ ፰ ፥፲፪ ፣ ፱ ፥ ፭ ። ፀሐይ በመዓልትና በሌሊት መካከል እንደምትለይ ፥ ፀሐየ ጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስም ፦ ጻድቃንን ከኃጥአን ፥ ኃጥአንን ከጻድቃን ይለያል። « የሰው ልጅ ( ወልደ ዕጓለ እመሕያው ክርስቶስ ) በጌትነቱ ቅዱሳን መላእክትን ሁሉ አስከትሎ በሚመጣበት ጊዜ ፥ ያን ጊዜ በጌትነቱ ዙፋን ይቀመጣል። አሕዘብ ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ ፥ እረኛም በጎችን ከፍየሎች እንደሚለይ እየራሳቸው ይለያቸዋል። በጎችን ( ጻድቃንን ) በቀኙ ፍየሎችንም (ኃጥአንን) በግራው ያቆማቸዋል። » ይላል ። ማቴ ፳፭ ፥ ፴፩። ፀሐይ የዕለታት ፥ የአራቱ አዝማናትና የዓመታት መለያ እንደሆነች ፦ እነዚህን ለይቶ ባርኮ የሰጠን ፀሐየ ጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። « ወትባርክ አክሊለ ዓመተ ምሕረትከ ፥ ወይጸግቡ ጠላተ ገዳም ፥ ወይረውዩ አድባረ በድው ፤ የምሕረትህን ዓመት አክሊል ትባርካለህ ፥ ምድረ በዳዎችም ጠልን ይጠግባሉ ፥ የምድረ በዳ ተራሮች ይረካሉ ፤ » ያለው ለዚህ ነው። መዝ ፷፬ ፥ ፲፩ ። አክሊል ያለው ፍሬ የሚሸከመውን የስንዴ ዛላ ነው። አክሊል የሚቀመጠው በራስ ላይ እንደሆነ ሁሉ ፍሬው ፥ ዛላው ከላይ ነውና።
፪ ፥ ፪፦ ቅዱሳን ፀሐይ ናቸው፤
          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዓለም ለይቶ የጠራቸውን ፥ ጠርቶም የመረጣቸውን ደቀመዛሙርቱን ፦ እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ  ፥ በተራራ ላይ የተሠራች ከተማ መሰወር አይቻላትም። » ብሏቸዋል። ማቴ ፭ ፥ ፲፬። እርሱ ፦  « እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ ፤ » ማለቱ የባህርዩ ሰለሆነ ነው ፥ የእነርሱ ግን የጸጋ ነው። በጸጋ ያከበራቸውም እርሱ ነው። በተጨማሪም ፦ « ያንጊዜም ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ያበራሉ ፤ ( ከፀሐይ ሰባት እጅ ያበራሉ ) ፤ » ብሏል። ማቴ ፲፫ ፥ ፵፫ ። በመሆኑም ቅዱሳን ባሉበት ቦታ ሁልጊዜ ብርሃን ነው። ጨለማ ይወገዳል።
          ቅዱስ ዮሐንስ « ብእሲት እንተ ትለብስ ፀሐየ፤ » ፀሐይን ተጐናጽፋ ያየው እመቤታችንን ነው። ክብሯን ፥ ልዕልናዋን ፥ ጸጋዋን እንደ ጸሐይ በሚያበራና በሚያንጸባርቅ ፥ ዓይንን በሚያጥበረብርና በሚበዘብዝ የወርቅ መጐናጸፊያ መልክ አይቷል። ፀሐይን መልበሷ ክብሯ ፀሐየ ጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ያመለክታል። በመሆኑም ክብሯን ማወቅ እርሱን ማወቅ ነው። ለቅዱሳን ሲሆን ደግሞ ክብራቸው እርሷ መሆኗን ያሳያል። ለምሳሌ የእኔን የተርታውን ቄስ ካባ ፓትርያርኩ ቢለብሱት ክብሩ ለእኔ እንጂ ለርሳቸው አይደለም ። እንግዲህ የእመቤታችን ክብሯ በሰማይ ከፍ ብሎ መታየቱ ክብርት ልዕልት እንድንላት መሆኑን አውቀን ከእግዚአብሔር በታች ከፍጡራን በላይ አድርገን ልናመሰግናት ይገባል። ቅዱስ ዳዊትም ከሁሉ አስቀድሞ ይህ ክብሯ ስለተገለጠለት ፦ « ወትቀውም ንግሥት በየማንከ ፥ በአልባሰ ወርቅ ዑፅፍት ወኁብርት ፤ በወርቅ ልብስ ተጎናጽፋና ተሸፋፍና( ወርቀ ዘቦ ግምጃ ደርባ ደራርባ ፥ ለብሳ ተጐናጽፋ ) ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች። ( ትገለጣለች ፥ በወርቅ ዙፋን ተቀምጣ ትታያለች ) ብሏል። መዝ ፵፬ ፥ ፱።
  « ጨረቃንም ከእግሯ በታች የተጫማች ፤»
          ጨረቃ የተፈጠረው ሌሊትን እንዲገዛ ነው። « ለጨረቃና ለከዋከብት ሌሊትን ያስገዛቸው ምሕረቱ ለዘላለም ነውና ፤ » ይላል። መዝ ፩፻፴፭ ፥ ፱ ፣ ዘፍ ፩ ፦ ፲፮ ። በተጨማሪም ፦ « ወገበርከ ወርኃ በዕድሜሁ ፤ ጨረቃን በጊዜው ፈጠርህ ፤» የሚል አለ። መዝ ፩፻፫  ፥ ፲፱። የጨረቃ ብርሃን ከፀሐይ ብርሃን አንድ ሰባተኛ ነው። ይኽንንም የፀሐይ ፥ የጨረቃና የከዋክብት ምሥጢር የተገለጠለት ሄኖክ ፦ « ከዚህ ሥርዓትም በኋላ ስሙ ጨረቃ የሚባል የታናሹን ብርሃን ሌላ ሥርዓት አየሁ። ክበቡም እንደ ሰማይ ክበብ ነው ፥ የሚሄድበትንም ሠረገላ ነፋስ  ይነዳዋል። ብርሃንም በመጠን ይሰጠዋል። በወሩም ሁሉ መውጫውና መግቢያው ይለወጣል ፥ ቀኑን እንደ ፀሐይ ቀን ነው። የብርሃኑ ሁኔታም በተስተካከለም ጊዜ የብርሃኑ መጠን ከፀሐይ ብርሃን ሰባተኛ እጅ (1/7) ይሆናል። » በማለት ነግሮናል። ሄኖ ፳፪ ፥ ፩። ጨረቃ ብርሃኗን የምታገኘው ከፀሐይ ነው። ጨረቃ ሙሉ ሆና ትወለድና ( ትታይና ) እያጸጸች ( እየጎደለች ) ሄዳ ትጠፋለች። እንደጠፋችም አትቀርም ፥ ተመልሳ ሙሉ ሆና ትወለዳለች። ይህም መወለዷ የመወለዳችን ፥ እያጸጸች ሄዳ መጥፋቷ ኑረን ኑረን የመሞታችን ፥ እንደገና መወለዷ የመነሣታችን ምሳሌ ነው።
          ቅዱስ ዮሐንስ እመቤታችንን « ወወርኀ ታሕተ እገሪሃ ፤ » እንዲል ጨረቃን ተጫምታ አይቷል። ጨረቃ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ናት። ጨረቃ ብርሃኗን ከፀሐይ እንድታገኝ ቤተ ክርስቲያንም ብርሃኗ ፀሐየ ጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እንዲሁም ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ፦ « ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ያበራሉ፤ » ያለላቸው ቅዱሳን ናቸው። ቤተ ክርስቲያን ሰማያዊ ጸጋ ያላት ፥ የመንፈስ ቅዱስ መዝገብ ቤት የሆነች ፥ በምድር ያለች የእግዚአብሔር መንግሥት ናትና ።
          ወደ ጨረቃዋ ምሥጢር ስንመለስ ፦ ደግሞ « ጨረቃ ከእግሯ በታች የተጫማች ፤ » የሚለው ትርጉም ቤተ ክርስቲያን ተብለው የሚጠሩ ምዕመናን ከእግሮቿ በታች ወድቀው ይሰግዱላታል ፥ ይገዙላታል ማለት ነው። ይኸውም ስለ ክርስቶስ ነው። ምክንያቱም በድንግልና ፀንሳ በድንግልና ወልደዋለችና። እንኳን የሚወዳት ይጠሏት የነበሩ እንኳ ወደ ልቡናቸው ተመልሰው ይሰግዱላታል። ይኽንንም ነቢዩ ኢሳይያስ ፦ « የአስጨናቂዎችሽም ልጆች ወደ አንቺ ይመጣሉ ፥ የናቁሽም ሁሉ ወደ እግርሽ ጫማ ይሰግዳሉ ፤ የእግዚአብሔር ከተማ ፥  የእስራኤል ቅዱስ ይሉሻል። » በማለት ነግሮናል። ኢሳ ፷ ፥ ፲፬ ። በተጨማሪም ፦ « ነገሥታትም አሳዳጊ አባቶችሽ ይሆናሉ ፥ እቴጌዎቻቸውም ሞግዚቶችሽ ይሆናሉ ፥ ግንባራቸውንም ወደ ምድር ዝቅ አድርገው ይሰግዱልሻል ፥ የእግርሽንም ትቢያ ይልሳሉ ፤ » የሚል አለ ። ኢሳ ፵፱ ፥ ፳፫ ።
፬ ፦« በራስዋ ላይ የአሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት ፤ »
፬ ፥ ፩፦ አክሊል
           አክሊል ፦ የክብር ምልክት የክብር መጨረሻ ነው። የሚቀዳጁትም ትልቅ ማዕረግና ታላቅ ክብር ያላቸው ሰዎች ናቸው። እግዚአብሔር አሮንን እና ልጆቹን ለክህነት ከለያቸው ( ከመረጣቸው ) በኋላ መፈጸም የሚገባውን ሥርዓት ለሙሴ ሲነግረው ፦ «ወታነብር አክሊለ ዲበ ርእሱ ፥ ወታነብር ቀጸላ ዘወርቅ ዲበ አክሊሉ ፤ አክሊልንም በራሱ ላይ ታደርጋለህ ፥ የወርቁንም ቀጸላ በአክሊሉ ላይ ታኖራለህ ፤ » ብሎታል። ዘጸ ፳፱ ፥ ፮ ። ይህም ስለ ሊቀካህናቱ ክብር ነው። ስለ ታቦቱ ክብርም ፦ « በውስጥና በውጭም በጥሩ ወርቅ ለብጠው ፥ በእርሱም ላይ በዙሪያው የወርቅ አክሊል አድርግለት ፤ » ብሎታል። ዘጸ ፳፭፥፲፩።
          አክሊል ( ዘውድ ) የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ነው። የብዕለ ሥጋ ፍጻሜው ዘውድ እንደሆነ ሁሉ የብዕለ ነፍስም ፍጻሜ አክሊል  ( ዘውድ ) የምትባል መንግሥተ ሰማያት ናትና ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ « እኔ ፈጽሜ ግዳጄን ጨርሻለሁ ፥ የማርፍበት ዕድሜዬም ደርሷል። መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ ፥ ሩጫዬንም ጨርሻለሁ ፥ ሃይማኖቴንም ጠብቄአለሁ። እንግዲህ የክብር አክሊል ይቆየኛል ፤ ( መን ግሥተ ሰማያት ተዘጋጅታልኛለች )፤ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው እግዚአብሔር በዚያ ቀን ለእኔ ያስረክባል ፤ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም። » ብሏል። ፪ኛ ጢሞ ፬ ፥ ፮ - ፰። ይህም ፦ « እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን ፥ የሕይወት አክሊልንም እሰጥሃለሁ ።» ከሚለው ጋር አንድ ነው። ራእ ፫ ፥ ፲። 
          እንግዲህ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አክሊል ተቀዳጅታ መታየቷ ከፍጥረታት ሁሉ በላይ የሆነውን ክብሯን ፥ ማዕረጓን የሚመሰክር ነው። እርሷ መልዕልተ ፍጡራን መትህተ ፈጣሪ ናትና። በሌላ በኲል ደግሞ የነቢያት የሐዋርያት ፥ የጻድቃን የሰማዕታት ፥ የሊቃውንት የካህናትና የምእመናን አክሊል እርሷ ናት። ቅዱስ ኤፍሬም ፦ «አክሊለ ምክሕነ ፥ ወቀዳሚተ መድኃኒትነ ፥ ወመሠረተ ንጽሕነ ፤ የመመኪያችን ዘውድ ፥ የደኅንነታችን መጀመሪያ ፥ የንጽሕናችንም መሠረት ፤» በማለት በውዳሴ ዘሠሉስ የተናገረው ለዚህ ነው።
፬ ፥ ፪ ኮከብ
 ኮከብ፦ በቁሙ ሲተረጐም ፦ የብርሃን ቅንጣት ፥ የጸዳል ሠሌዳ ፥ ብርሃን የተሣለበት ፥ የሰማይ ጌጥ ፥ የጠፈር ፈርጥ ፥ ሌሊት እንደ አሸዋና እንደ ፋና በዝቶ የሚታይ ፥ የሚያበራ ፥ የፀሐይ ሠራዊት ፥ የጨረቃ ጭፍራ ማለት ነው። የተፈጠረውም ሌሊቱን እንዲገዛ በሌሊት እንዲሰለጥን ነው። መዝ ፩፻፴፭ ፥ ፱ ። ከዋክብት በሰዎች ዘንድ የማይቆጠሩ ናቸው። በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ቁጥራቸው ይታወቃል ፥ በየስማቸውም ይጠራቸዋል። መዝ ፩፻፵፮ ፥ ፬ ። እግዚአብሔር አብርሃምን ወደ ሜዳ አወጣውና ፦ « ወደ ላይ ወደ ሰማይ ተመልከት ፥ ልትቆጥራቸው ትችል እንደሆነ ከዋክብትን ቊጠራቸው ። ዘርህም እንደዚሁ ነው። » ብሎታል። ዘፍ ፲፭ ፥ ፭። በከዋክብት የተመሰሉት ከአብርሃም ወገን የሚወለዱት ቅዱሳን ነገሥታት ፥ ቅዱሳን ነቢያት ፥ ቅዱሳን ሐዋርያት ፥ ቅዱሳን ካህናት ፥ ቅዱሳን ሊቃውንት ፥ ቅዱሳን ምእመናን ናቸው። ይኸውም ይታወቅ ዘንድ ነቢዩ ዳንኤል ፦ « ጥበበኞችም እንደ ሰማይ ጸዳል ፥ ከጻድቃንም ብዙዎች እንደ ከዋክብት ለዛለዓለም ያበራሉ። » ብሏል። ዳን ፲፪ ፥ ፫። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ፦ « ኮከብ እምኮከበ ይኄይስ ክብሩ ፤ ኮከብ ከኮከብ ክብሩ ይበልጣልና፤ » ብሏል። ፩ኛ ቆሮ ፲፭ ፥ ፵፩ ።
          እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም « ወዲበ ርእሳኒ አክሊል ዘዐሠርቱ ወክልኤቱ ከዋክብት ፤ » አሥራ ሁለቱ ከዋክብት እንደ እንቊ ፈርጥ ያለበት አክሊል  ( ዘውድ ) በራሷ ላይ ተቀዳጅታ ( ደፍታ ) ታይታለች። አሥራ ሁለት መሆናቸው የአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ምሳሌ ነው። አንድም ከዋክብት ሌሊትን እንዲገዙ እርሷም የጨለማን አበጋዝ ዲያቢሎስን እስከነ ሠራዊቱ እንደምትገዛቸው ያመለክታል። በከዋክብት የተመሰሉ ሐዋርያትም ገዝተዋቸዋል። ማቴ ፲ ፥ ፩ ፣ ማር ፲፮ ፥ ፲፯።
፭ ፦ « ሴቲቱም ጸንሳ ነበረች፤ »
          ይህች ፀሐይን ተጐናጽፋ ፥ ጨረቃን ተጫምታ ፥ አሥራ ሁለት ከዋክብት እንደ እንቊ ፈርጥ ያለበት አክሊል ተቀዳጅታ የታየችው ሴት ፀንሳ ነበር። ይህ ሁሉ ክብር የተሰጣት ፦ ከእግዚአብሔር የተላከ ቅዱስ ገብርኤልና መንፈስ ቅዱስ ያደረባት ቅድስት ኤልሳቤጥ እንደመሰከሩት ፦ ከሴቶች ሁሉ ተለይታ የተባረከች በመሆኗ ነው። ( መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ ያልነበረባት ፥ እያማለደች በረከተ ሥጋን በረከተ ነፍስን የምታሰጥ ናት )።  ሉቃ ፩ ፥ ፳፰ ፣ ፵፪ ።
          እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የፀነሰችው በመንፈስ ቅዱስ ግብር ነው። በመሆኑም ቅድመ ፀኒስ ፥ ጊዜ ፀኒስ ፥ ድኅረ ፀኒስ ድንግል ናት። « ናሁ ድንግል ትፀንስ ፥ ወትወልድ ወልድ ፤ እነሆ ድንግል በድንግልና ትፀንሳለች ፥ ወልድንም ትወልዳለች ፤ » እንዳለ። ኢሳ ፯ ፥ ፲፬ ። እመቤታችን፦ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል፦ « ወናሁ ትፀንሲ ፥ ወትወልዲ ወልደ ፤ ወትሰምዪዮ ስሙ ኢየሱስ። እነሆ በድንግልና ትፀንሻለሽ ፥ ወልድንም ትወልጃለሽ ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ ። » ባላት ጊዜ ፥ «እም አይቴ ረከብከ ዘከመዝ ብሥራተ ፥ ዘእንበለ  ምት እምድንግል ፅንሰተ ፤ ወዘእንበለ ዘርዕ እምድር ዕትወተ። ምድር ያለ ዘር ታፈራ ዘንድ ፥ ሴት ያለ ወንድ ትፀንስ ዘንድ ፥ እንዲህ ያለ የምሥራች ከማን አገኘኸው ? » ብላዋለች። እርሱም ፦ « ያንቺ ፅንስ እንደ ሌሎች ሴቶች ፅንስ አይደለም። መንፈስ ቅዱስ ያድርብሻል ፥ ኃይለ ለዑል ወልድም ሥጋሽን ይለብሳል። » ብሏታል። ሉቃ ፩ ፥ ፴፩ ፣ ፴፬
፮፦ « ለመውለድም ምጥ ተይዛ ትጮህ ነበር፤ »
          « ምጥ » የመጣው ከበደል በኋላ በእርግማን ነው። እግዚአብሔር ሔዋንን ፦ « አብዝኆ አበዝኆ ለኃዘንኪ ወለሥቃይኪ ፥ ወበፃዕር ለዲ ኲሎ መዋዕለ ሕይወትኪ። ኃዘንሽን ፥ ፃዕርሽን አበዛዋለሁ ፤ በምትወልጂበት ጊዜ ሁሉ በፃር በጋር ውለጂ። » ብሏታል። ዘፍ ፫ ፥ ፲፮ ።
          እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ግን የአዳምና የሔዋን መርገም ያልወደቀባት ንጽሕት ዘር ናት ። በመሆኑም ፃር ጋር አልነበረባትም። ከሴቶች ሁሉ ተለይታ የተባረከች በመሆኗ መንፈስ ቅዱስ ከልማደ አንስት ጠብቋታል። የሚያስምጥ የሚያስጨንቅ በዘር በሩካቤ ተፀንሶ የሚወለድ ነው። የእመቤታችን ፅንስ ግን እንበለ ዘርዕ በመንፈስ ቅዱስ በድንግልና ፥ የምትወልደውም በድንግልና በመሆኑ ምጥ ፥ ጭንቅ የለም።
          ታዲያ ፦ « ለምን ? ለመውለድም  ምጥ  ተይዛ ትጮህ ነበር ፤ » አለ ፥ እንል ይሆናል። ምጥ ያለው፦ ነፍሰ ጡር ሆና ለመቆጠር እስከ ዳዊት ከተማ እስከ ቤተልሔም መጓዟን ፥ ማደሪያ አጥታ በከብቶች በረት አድራ መውለዷን ፥ በሄሮድስ ምክንያት መሰደዷን ፥ በአጠቃላይ በአይሁድ የዘወትር ጥላቻ የደረሰባትን መከራ ነው። ምክንያቱም ጽኑዕ መከራ ምጥ ይባላልና ነው።
-       « አቤቱ በመከራዬ ጊዜ አሰብኹህ ፥ በጥቂት መከራም ገሠጽኸኝ። የጸነሰች ሴት ለመውለድ ስትቀርብ እንደምትጨነቅና በምጥ እንደምትጮህ ፥ አቤቱ ፥ እንዲሁ በፊትህ ለወዳጅህ ሆነናል። አንተን በመፍራት አቤቱ ፥ እኛ ፀንሰናል ፥ ምጥም ይዞናል። » ኢሳ ፳፮ ፥ ፲፮።

-       « አሁንስ ለምን ክፉ መከርሽ ? እንደምትወልዽ ሴት ምጥ የደረሰብሽ ፥ ንጉሥ ስለሌለሽ ነውን? ወይስ መካሪ ስለጠፋብሽ ነውን? የጽዮን ሴት ልጅ ሆይ እንደምትወልድ ሴት አምጪ ፥ ታገሺም ፤ አሁን ከከተማ ትወጪያለሽና ፥ በሜዳም ትቀመጫለሽ ፥ ወደ ባቢሎንም ትደርሻለሽ ፥ በዚያም ያድንሻል። » ሚክ ፩ ፥ ፱።

-       « ሕዝብ በሕዝብ ላይ ፥ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣሉ ፤ በየሀገሩም ረኃብ ፥ ቸነፈርም ፥ የምድር መናወጥም ይሆናል። እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው። » ማቴ ፳፬ ፥ ፯ ።

፯፦ « ሌላም ምልክት በሰማይ ታየ ፤ ራእ ፲፪ ፥ ፫ . . . . . . . . .

7 comments:

 1. Egziabher yibarkelen. Amen!

  ReplyDelete
 2. OMG ALU YENY CASTEMER
  ENDET DES YELALE ENDHE NEW ENG KEWNEMA
  YEBELU KECECE BERHANU YEKETLU.
  SELAME LEHULACHEN

  ReplyDelete
 3. እመቤታችን ጣእሟን ፍቅሯን ታሳድርቦት ታሳድርብን።

  ReplyDelete
 4. +++

  አባታችን ቃለ ህይዎት ያሰማልን:: እመቤታችን በምልጃዋ ቤተሰበዎን አትለይ::

  ልቦና ይስጠን እንጅ የቤተክርስቲያን ትምህርት ቤቱን አግኝቶአል እና በርቱልን አባታችን::

  ረዴተ እግዚአብሔር አይለየን

  ReplyDelete
 5. ቃለ ሕይወትን ያሰማልን!
  አመአምላክ በረዴት አትለየን።

  ReplyDelete
 6. amennnnnnnnnnnnnnnnnn!!!!!!!!!!!!!!!

  ReplyDelete
 7. ለአፍ የሚጣፍጥ ፥ ልቦናን የሚመስጥ ፥ህይወትን የሚያንጽ የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ክብር የሚገልጽ የህይወት ምግብ ነው የመገቡን ። ቃለ ህይወት ያሰማልን

  ገ/ሥላሴ ከ አንጐላ

  ReplyDelete